Fana: At a Speed of Life!

በአሜሪካ ቴክሳስ በአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች እና መምህራን ላይ የተፈጸመው ግድያ ቁጣ አስነሳ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት በአንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ 19 ተማሪዎች እና ሁለት መምህራን ላይ የተፈጸመው ጅምላ ግድያ በህዝብ ዘንድ ቁጣና የተቃውሞ ሰልፍ ማስነሳቱ ተግልጿል።

ሰልፈኞቹ በጥይት የተገደሉ ተማሪዎችን ፎቶግራፎች ይዘው “ብሔራዊ የጠብመንጃ ማኅበርን አንፈልግም”፣ “የተገደሉት ልጆቻችሁ ቢሆኑ ኖሮስ ” የሚሉ እና ሌሎች መሰል ይዘት ያላቸው መፈክሮችን ይዘው ተቃውሟቸውን አሰምተዋልል፡፡

ቴክሳስ ግዛት በምትገኘው ዩቫልዴ በተሰኘችው ትንሽ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በ 18 ዓመቱ ወጣት የተፈጸመው ግድያ “ኤ አር 15” በተሰኘ ከፊል አውቶማቲክ ጠብመንጃ የተፈጸመ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በነገው ዕለት በሚኖረው መርሐ ግብር ጅምላ ግድያ በተፈጸመበት ትምህርት ቤት ተገኝተው የሟቾችን ቤተሰቦች እንደሚያጽናኑ ተነግሯል፡፡

በጉዳዩ ላይ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰጡት አስተያየት፥ ለተፈጸመው ጥቃት ዴሞክራቶችን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

የትምህርት ቤቶች የደኅንነት ሁኔታ በድጋሚ እንዲጤንና ከመሰል አደጋዎች እንዲጠበቁም የጠየቁት ትራምኝ፥ በሀገሪቷ ያለው የአዕምሮ ጤና አጠባበቅ እና ክትትል ሁኔታ መጤን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

መምህራን ሥልጠና አግኝተው ወደ ክፍል በድብቅ የሚገቡ የጦር መሳሪያዎችን መያዝ እንዲችሉ መፈቀድ እንዳለበት ዶናልድ ትራምፕ መናገራቸውንም ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡

ሪፐብሊካኗ የደቡብ ዳኮታ ገዢ ክርስቲ ኖኤም፣ ተቃዋሚዎቹ ከመሣሪያ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ የሚያደርጉትን ትግል እንዳያቆሙ ያሳሰቡ ሲሆን ፣ ሪፐብሊካኑ የቴክሳስ ገዢ ግሬግ አቦት በትዕይንተ ህዝቡ ላይ በመገኘት ለሟች ቤተሰቦች ሐዘናቸውን እንደገለጹ ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል የተቃውሞ ትዕይንተ-ህዝቡ በሚካሄድበት አቅራቢያ ባለ ሕንጻ ውስጥ ፣ የጅምላ ግድያው ከተፈጸመ ከ ሦስት ቀናት በኋላ ፣ የአሜሪካው ብሔራዊ የጠብመንጃ ማኅበር ዓመታዊ ስብሰባውን እያካሄደ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.