Fana: At a Speed of Life!

የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት በመደበኛ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት በመደበኛ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ውስጥ በተደራጀ መልኩ እንዲካተቱ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ያዘጋጀው ሁለተኛው አገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ምስለ-ችሎት ውድድር በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በዚሁ መርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ እንደጠቆሙት÷በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለመቀነስ ከታችኛው ክፍል ጀምሮ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ሊከናወነ ይገባል፡፡

በመሆኑም ኮሚሽኑ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት እንደ አንድ መደበኛ የትምህርት ዓይነት በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ኮሚሽኑ አዲስ ስትራቴጂ ነድፎ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ሰፊ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዛሬ የተካሄደው ሁለተኛው ዙር የምሰለ-ችሎት ውድድር የዚሁ ስራ አካል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በውድድሩ ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ 63 ትምህርት ቤቶች ተሳታፊ መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡

በውድድሩ 130 ተማሪዎች መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ ተሳታፊዎቹ በውድድሩ ከመሳተፍ ባሻገር ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ውድድሩ ስለሰብዓዊ መብት በቂ ግንዛቤ ያላቸውና ለነገ ራዕይ የሰነቁ ወጣቶችን በማፍራት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ዋና ኮሚሽነሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የውድድሩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ውድድሩ ስለሰብዓዊ መብቶች ያላቸውን ግንዛቤ እንዳሻሻለላቸው ነው የተናሩት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.