“የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለአዲስ አበባ ወጣቶች የአንድነት ማሳያ ነው” – ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለአዲስ አበባ ወጣቶች የሰላም፣ የአንድነትና የአብሮነት ማሳያ ነው” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
“አዲስ አበባ የሰላምና የአብሮነት ከተማ” በሚል መሪ ቃል ከተማ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በዚሁ መርሐ ግብር የተገኙት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ÷ “ይህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለአዲስ አበባ ወጣቶች የሰላም፣ የአንድነትና የአብሮነት ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ ምንጊዜም ቢሆን ለስርዓት አልበኝነት እና ለመከፋፈል ምቹ አይደለችም ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ ወጣቶችም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ስታደርጉ ከተማችን ለስርዓት አልበኝነት አትመችም፣ አብሮነቷ ይቀጥላል፣ አንድነቷ ያብባል እያላችሁ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና በዓለም አቀፍ ደረጃ የምታኮራን እንድትሆን እናደርጋታለን ያሉት ወይዘሮ አዳነች÷ ይህንንም ማንም ሊያስቆመን አይችልም፣ ልጆቿ በትጋት እንሰራለን ብለዋል፡፡
ጤናማ፣ ብቁና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ስፖርት ያለውን ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት እንዲሁም ስፖርትን በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በየሳምንቱ በቋሚነት እያዘጋጀ መሆኑን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡