የዝንጀሮ ፈንጣጣ “በመካከለኛ” ደረጃ የዓለም የጤና ሥጋት መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዝንጀሮ ፈንጣጣ በመካከለኛ ደረጃ የዓለም የጤና ሥጋት መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ፡፡
ቫይረሱ ሥጋት ሊሆን የሚችለው ለከባድ በሽታ ተጋላጭ ወደሆኑ ሕፃናት ከተዛመተ እና የበሽታ መከላከል አቅማቸው ወደተዳከመ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከተሠራጨ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አመላክቷል።
ከፈረንጆቹ ግንቦት 26 ጀምሮ 23 ሀገራት በድምሩ 257 በዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፥ 120 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሳይያዙ አልቀረም የሚል ጥርጣሬ እንዳለ ድርጅቱ በመግለጫው አስታውቋል።
በቫይረሱ እስካሁን የተመዘገበ የሞት አደጋ የለም።
የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኙ ከዚህ ቀደም ተከስቶባቸው በማያውቁ ሀገራት ሳይቀር በአንድ ጊዜ መታየቱ በሽታው መከሰቱ ሳይታወቅ ተደብቁ መቆየቱን እንደሚያሳይ አመላካች ነው ብሏል፡፡
እንደ ድርጅቱ ገለጻ ቫይረሱ ተላላፊ በመሆኑ እስካሁን ባልታየባቸው ሀገራትም በቀጣይ ሊከሰት እንደሚችል ጠቁሞ የሚያሰጋ ገዳይ በሽታ ባለመሆኑ ሰዎች ሳይጨነቁ በተቻለ መጠን ራሳቸውን ከንክኪ በማራቅ የግል ንፅሕናቸውን እንዲጠብቁ ማሳሰቡን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡