የሶማሌ ክልል መንግስትና የዓለም ምግብ ፕሮግራም የመሰረተ ልማት ትብብሮችን ማጠናከር በሚችልበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 22 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በኢትዮጵያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር ጋር በመሰረተ ልማት ትብብር ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም የክልሉን ህዝብ ኑሮ ለማሻሻልና የግብርና ልማትን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸው ነው የተገለጸው፡፡
አቶ ሙስጠፌ የክልሉ ህዝብ ከውጪ ከሚገባ ምግብ ጥገኝነት በመላቀቅና ማህበረሰቡ በአገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት ላይ እንዲያተኩር እና የአገር ውስጥ ግብርና ምርቶችን የማሳደግ ባህል እንዲዳብር በታቀዱ ስትራቴጂዎች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በሶማሌ ክልል በተደጋጋሚ ለሚከሰተው ድርቅና የተፈጥሮ አደጋዎች በዘላቂነት ለመቋቋም የዓለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ እየተከናወነ የሚገኘው የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮና የመስኖ ልማት ሥራዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ክላውድ ጂቢዳር በበኩላቸው÷ መንግስት በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ማህበረሰቡ ወደ ግብርና ሥራዎች እንዲያመራ ለታለመው ዕቅድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሚያደርግ መናገራቸውን ከሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡