በህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ የውጭ አካል ጣልቃ ገብነት እና ጫና ተገቢነት የሌለው ነው – አቶ ደመቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “በህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ይህን አድርጉ፣ ይህን አታድርጉ፣ ይህንን ፈርሙ የሚል ዓይነት አካሄድ ተገቢነት የሌለውና ድፍረት የተቀላቀለበት አካሄድ” መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት 12ኛ መደበኛ ጉባዔውን አካሂዷል።
በጉባዔው ላይም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተርር ኢንጂነር ስለሺ በቀለን ጨምሮ ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ተገኝተዋል።
የብሔራዊ ምክር ቤቱ አባላት በጉባዔው ላይ በተለይም የአሜሪካ መንግስት ሰሞኑን ያሳየውን አቋም በማንሳት አሜሪካ ወደ ድርድር ሂደቱ ለምን ገባች፣ የሱዳን አቋም ምንድን ነው፣ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ረገድ እየተሠራ ስላለው ሥራ እና መረጃን ለሕዝቡ በማቅረብ ረገድ በመንግሥት በኩል ክፍተት አለ የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን፥ ኢትዮጵያን በዳይ አድርጎ የማቅረብና ሌሎቹን በደጋፊነት የማሰባሰብ ሁኔታ ስለነበረ እውነታውን ለማስረዳት ሲባል አሜሪካና የዓለም ባንክ በታዛቢነት በሚሳተፉበት ድርድር ኢትዮጵያ መግባቷን ጠቁመዋል።
አሁን ግን ይህን አድርጉ፣ ይህን አታድርጉ ይህንን ፈርሙ የሚል ዓይነት አካሄድ ተገቢነት የሌለውና ድፍረት የተቀላቀለበት አካሄድ ስለሆነ መታረም አለበት ማለታቸውን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
ቀጣይ የድርድር ሂደቶችም በጥበብ፣ የኢትዮጵያን ጥቅም በማስጠበቅና በማረጋጥ መሆን እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
የህዳሴው ግድብ የተጀመረበት 9ኛ ዓመት ወደፊት በሚከበርበት ሁኔታም በሁሉም ክልሎች ሕዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር፣ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በተለይም በአባይ ተፋሰስ ውስጥ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
በጉባዔው ላይ ግድቡ አሁን የደረሰበት የግንባታ ደረጃና የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት የሶስትዮሽ ድርድርን በተመለከተ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ለብሔራዊ ምክር ቤቱ አባላት ገለጻ አድርገዋል።
በተለይም በድርድሩ ሂደት የአሜሪካ ከታዛቢነት ወደ አሸማጋይነት ብሎም ስምምነት አርቃቂነት የተሸጋረችበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው፥ በኢትዮጵያ በኩል ይህ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ለምክር ቤቱ አባላት አረጋግጠዋል።
በግብጽ በኩል ድርድሩ ከሕዳሴው ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ አልፎ በውሃ ድርሻና አጠቃቀም ላይ እንዲሆንና የኢትዮጵያን የወደፊት በአባይ ውሃ የመጠቀም መብትን የሚገድብ ዓይነት ስምምነት ላይ እንዲደረስ ፍላጎቶች እንዳሉም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ በኩል ከሕዳሴው ግድብ ውሃ አለቃቀቅና አሞላል ውጭ የሚደራደሩበት ጉዳይ እንደሌለም አብራርተዋል።