በጁባ በዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪዎች መካከል በተካሄደ የሩጫ ወድድር ወታደር ባንተ ዕድል ይታየው አሸነፈ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ሱዳን ጁባ ከ120 ሀገራት የተውጣጡ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር አባላት መካከል በተካሄደ የ12 ኪሎ ሜትር የሩጫ ወድድር ኢትዮጵያዊው ወታደር ባንተዕድል ይታየው አሸነፈ፡፡
በውድድሩ ኢትዮጵያን በመወከል የ15ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አሰከባሪ ሻለቃ አባል ወታደር ባንተዕድል ይታየው ውድድሩን በአንደኝነት በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
በውድድሩ በክብር እንግድነት ተገኝተው ሽልማቱን ያበረከቱት በጁባ የዓለም አቀፉ ሰላም አስከባሪ ኃይል የበላይ ጠባቂ ጀኔራል ኒኮላስ ሃይከን ባስተላለፉት መልዕክት÷ የየሃገራቱ ሰላም አስከባሪ ሻለቆች በአስቸጋሪ የአየር ፀባይና መልክአምድር ከግዳጃቸው ጎን ለጎን ለስፖርት የሰጡት ትኩረት ያስመሰግናል ብለዋል፡፡
ጀኔራል መኮንኑ ሰላም አስከባሪ ሻለቃዎች ለአለም ሰላም በማስፈን የየሀገራቸው አምባሳደሮች መሆናቸውን ጠቁመው÷ ስፖርታዊ ውድድሩ የሃገራቹሁን ባህል ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ስለሚፈጥር አጠናክራችሁ ልትቀጥሉ ይገባል ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ 15ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃን ወክሎ የተወዳደረው አትሌት ወታደር ባንተ ዕድል ይታየው÷ በውድድሩ ትልቅ ልምድና ተሞክሮ ያገኘበት መሆኑን በመገልፅ በቀጣይም ሀገሬን እና ተቋሜን ለማስተዋወቅ ጠንክሬ እሰራለሁ ብሏል።