ከ8 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 22 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከውጭ አገር ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከ8 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ አገር ውስጥ ተጓጉዞ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ።
ኮርፖሬሽኑ ለ2014/15 የሰብል ምርት ዘመን 12 ሚሊየን 876 ሺህ 623 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ገዝቻለው ብሏል።
ከዚህ ውስጥ ከጥር ወር ጀምሮ እስከ ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ 9 ሚሊየን 829 ሺህ 190 ኩንታል የተለያዩ የአፈር ማዳበሪያ ዓይነቶች ጅቡቲ ወደብ መድረሳቸው ነው የተገለጸው።
ከዚህም 8 ሚሊየን 243 ሺህ 689 ወይም 84 በመቶው ወደ አገር ውስጥ ተጓጉዞ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጋሻው አይችሉህም ተናግረዋል።
ለዘንድሮ የሰብል ዘመን ከሞሮኮው የአፈር ማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ኦ ሲ ፒ የተገዛውን የ ኤን ፒ ኤስ ዓይነት ማዳበሪያ ወደ ጅቡቲ ወደብ የማጓጓዝ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል ብለዋል።
በሌላ በኩል ከውጭ አገር ከተገዛው 5 ሚሊየን 1 ሺህ 100 ኩንታል ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ በአራት ዙር ጅቡቲ ወደብ የተራገፈው የዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ መጠን 1 ሚሊየን 953 ሺህ 670 ኩንታል ደርሷል ነው ያሉት።
ከሁለት ቀናት በኋላ ተጨማሪ 450 ሺህ ኩንታል ዩሪያ ወደብ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት ኃላፊው÷ ኮርፖሬሽኑ ለዘንድሮ የሰብል ዘመን የገዛው 12 ሚሊየን የአፈር ማዳበሪያ ኦሲ ፒ እና ፈርቲ ግሎብ ከተሰኙ ዓለም አቀፍ የአፈር ማዳበሪያ አምራች ኩባንያዎች መሆኑንአንስተዋል።
ለዘንድሮ የሰብል ዘመን ከሞሮኮው ኦ ሲ ፒ ኩባንያ የተገዛው 7 ሚሊየን 875 ሺህ 523 ነጥብ 4 ኩንታል ኤን ፒ ኤስ የአፈር ማዳበሪያ ዓይነት፥ በ13 መርከቦች ተጓጉዞ ሙሉ በሙሉ ጅቡቲ ወደብ ደርሷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በአሁኑ ወቅት ባለፈው ሣምንት የመጨረሻዋ መርከብ ያራገፈችው ኤን ፒ ኤስ እና ኤን ፒ ኤስ ቢ ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ እየተጓጓዘ መሆኑም ተመላክቷል፡፡