ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ከተባበሩት መንግስታት የ ዩኤን ሃቢታት የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 26 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ከተባበሩት መንግስታት ዩ ኤን ሃቢታት የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ኦማር ሳይላ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይታቸው በሚኒስቴሩ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫዎችና በከተማ ልማት ቀዳሚ አጀንዳዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነበር።
በወቅቱም በተያዘው የፈረንጆቹ 2020 መጨረሻ ድረስ በሚከናወኑና የዕቅዱን ተፈፃሚነት የሚያፋጥኑ ጉዳዮችን በመለየት በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።
በመሬት አስተዳደር ብቃት ማረጋገጥ፣ ለካዳስተር ስራዎች አስፈላጊ በሆኑ መሳሪያዎች፣ የከተማ ልማት መረጃዎች የመነሻ ጥናትና በዘርፉ ቀዳሚ አጀንዳዎች የተፈጻሚነት ጥናት
ማስጀመርን በተመለከተ ውይይት አድርገዋል።
በተባበሩት መንግስታት የዩ ኤን ሃቢታት የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ኦማር ሳይላ የ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድና በቀዳሚ አጀንዳዎች ዙሪያ የተቀመጡትን ጉዳዮች፥ ከተቋሙ ፕሮጀክቶች ጋር በማጣጣም መስራት የሚቻልበትንና ድጋፍ የሚገኝበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ዩ ኤን ሃቢታት ካሉት ዘጠኝ ፕሮግራሞች ከ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ ጋር አጣጥሞ ለመከለስና አብሮ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረምም ስምምነት ደርሰዋል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ በአፋጣኝ ወደ ተግባር የሚገባበትንና ሴክተሩ በከፍተኛ ቴክኒካል ባለሙያዎች መደገፍ በሚችልበት ሁኔታ መወያየታቸውን ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision