Fana: At a Speed of Life!

ቡናን በኮንቴይነር አሽጎ በመሸጥ የተገኘው ስኬት በቅባት እህሎችና ጥራጥሬ ምርቶች ላይ  ሊደገም ይገባል- ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቡናን በዲጂታል ሥርዓት ታግዞና በኮንቴይነር አሽጎ በመሸጥ (ኮንቴነራይዜሽን) የተገኘው ስኬት በቅባትና በጥራጥሬ ምርቶች ላይ ሊደገም እንደሚገባ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር እና የብሔራዊ ሎጂስቲክስ ምክር ቤት ሰብሳቢ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ አሳሰቡ፡፡

10ኛው የብሔራዊ ሎጂስቲክስ ምክር ቤት ጉባኤ የ2014 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

በግምገማው ላይም÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴው በወደብ አጠቃቀም እና በኮንቴነራይዜሽን ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱ ተገልጿል፡፡

የሞምባሳ/ሞያሌ ኮሪደርን በሙከራ ደረጃ በተያዘው ዓመት ወደ ስራ ማስገባት መቻሉ እንዲሁም የታጁራ ወደብ አገልግሎት መስጠት መጀሩ የወደብ አማራጮችን ከፍ እንዲል ማድረጉም ተመላክቷል፡፡ በዚህም የሎጅስቲክስ ጊዜና ወጪ እየቀነሰ መጥቷል ነው የተባለው፡፡

የሎጂስቲክስ ትራንስፎርሜሽን ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ አቶ እውነቱ ታዬ÷ የብሔራዊ ካውንስሉ ከፍተኛ ግፊት በማድረጉ እና የወደብ አማራጮች ጥቅም ላይ መዋላቸው ከተገኙ  ስኬቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በባቡር የሚደረግ የገቢና ወጪ ዝውውር እንዲጨምር መደረጉ፣ ሸቀጦችን በኮንቴነር አሽጎ መላክ መቻሉ እና በሌሎችም ተግባራት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ2 ነጥብ 32 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉም ተመላክቷል፡፡

ቀደም ሲል ባልተደራጀ መልክ ይጓጓዝ የነበረው ቡና በሀገር ውስጥ በኮንቴነር አሽጎ ወደ ወደብ ማጓጓዝ መጀመሩና በዚህም 97 ነጥብ 70 ከመቶ በኮንቴነር  ታሽጎ መላኩም ነው የተገለጸው፡፡ በዚህም ቅሸባን በማስቀረትና የሚወስደውን የተራዘመ የጉዞ ጊዜ ጭምር ማሳጠር በመቻሉ  ስኬት እንዲመዘገብ አስችሏል ነው የተባለው፡፡

መድረኩን የመሩት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር እና የብሔራዊ ሎጂስቲክስ ምክር ቤት ሰብሳቢ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ÷ በቡና ኮንቴነራይዜሽን የተገኘው ስኬት በቅባትና በጥራጥሬ ምርቶች ላይ መድገም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ይህን ለማሳካት የምክር ቤቱ አባላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.