Fana: At a Speed of Life!

“ስለ ኢትዮጵያ” ሀገራዊ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “ስለ ኢትዮጵያ” ሀገራዊ የምክክር መድረክ “ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች ” በሚል መሪ ቃል በሐረር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ የኢትዮጵያውያን የጋራ እሴቶች ለሀገር ህልውና ባላቸው ሚና ላይ ያተኮሩ ሦስት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል።

ከፅሁፍ አቅራቢዎቹ መካከል የሀረሪ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ አቶ ተወላዳ አብዶሽ፥ የጋራ እሴቶቻችን ማወቅና ማጎልበት ለሀገራዊ አንድነትና እድገት መሠረት የሚጥል ስለመሆኑ ተናግረዋል።

እነዚህ ሀብቶችን በተገቢው ሁኔታ ማልማት ሲቻል የተፈለገው ሠላምና እድገት ማረጋገጥ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

የጋራ እሴቶቻችንን የህግ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል ያሉት ደግሞ የህግ መምህርሩና ጠበቃው አቶ ቀለመወርቅ ሚደቅሳ ናቸው።

ኢትዮጵያውያን ያላቸውን የልቡና ውቅር ጠብቆ ከማስቀጠል አንፃር የፌዴራልና የክልል ህጎች ይህንኑ ታላሚ አድረገው መውጣት እዳለባቸው አመላክተዋል።

የሥነ-መለኮትና ሥነ-ልቡና መምህሩ ዶክተር ወዳጄነህ መሀረነ በበኩላቸው፥ ÷ኢትዮጵያዊነት በሐረር ከተማ የሚመሰል፥ ማንም ሊያፈርሰው የማይቻለው የታጠረች ከተማ ነው” ብለዋል።

ይህችም የታጠረች ከተማ በልጆቿ አንድነት ተጠብቃ ዛሬ መድረሷን ጠቁመው፥ አሁን ያለው ትውልድም ይህንኑ ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ይገባዋል ነው ያሉት።

“ስለ ኢትዮጵያ ” የምክክር መድረክ በተለያዩ 11 ከተሞች እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡

በእዮናዳብ አንዱዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.