Fana: At a Speed of Life!

ቱርክ በፊንላንድ እና ስዊድን የኔቶ የአባልነት ጥያቄ ላይ የያዘችውን አቋም እንደማትቀይር አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2014 (ኤፍ በቢ ሲ) ቱርክ ለደህንነቷ እና ለኔቶ የወደፊት እጣ ፋንታ ስትል በፊንላንድ እና ስዊድን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የአባልነት ጥያቄ ላይ የያዘችውን አቋም እንደማትቀይር አስታወቀች።
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶኻን ሃገራቱ የኩርድ ሰራተኞች ፓርቲ (ፒ ኬ ኬ) ደጋፊዎች ናቸው በሚል ይወነጅሏቸዋል።
ከዚህ አንጻርም ቱርክ ለራሷ ደህንነት እና ለቃል ኪዳኑ የወደፊት ዕጣ ፋንታ ስትል የሃገራቱን አባልነት አትቀበልም ብለዋል።
ቱርክ የኔቶ አባል ሀገር እንደመሆኗ መጠን በአውሮፓ ህብረት እና በአሜሪካ ጭምር በአሸባሪነት የተፈረጀውን ፒ ኬ ኬን የሚደግፉ ሀገራትን ከኔቶ አባልነት የመከልከል ሙሉ መብት እንዳላትም አስረድተዋል።
ሽብርተኝነት የሁሉም አባላት ስጋት ስለሆነ ሀገራቱ ከመቀላቀላቸው በፊት ይህንን እውነታ ሊገነዘቡ ይገባል ማለታቸውን ቲ አር ቲ ዘግቧል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የኔቶ አባል ሀገራት አስፈላጊ እርምጃዎችን ካልወሰዱ በስተቀር ቱርክ በዚህ ጉዳይ ላይ አቋሟን አትቀይርም ብለዋል ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን፡፡
ሁለቱ ሃገራት ሩሲያ ታጠቃናለች በሚል ስጋት ኔቶን ለመቀላቀል በፈረንጆች ግንቦት 8 ይፋዊ የአባልነት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፥ የኔቶ አባል ሀገር የሆነችው ቱርክ ደግሞ ሀገራቱ አሸባሪ ድርጅቶችን ይደግፋሉ በሚል ጥያቄያቸውን መቃወሟ ይታወሳል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.