የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሠላም ጥሪን ተቀብለው የሚመለሱ የጉሙዝ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የሠላም ጥሪን ተቀብለው የሚመለሱ የጉሙዝ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ተናገሩ፡፡
በክልሉ መተከል ዞን ዳንጉርና ማንዱራ ወረዳዎች ወደ ጫካ ገብተው የነበሩ እና የክልሉን መንግስት የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 493 የጉሙዝ ወጣቶች በክልሉ ፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ የተሃድሶ ስልጠና ዛሬ መውሰድ ጀምረዋል፡፡
በዚሁ መርሐ ግብር የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ÷ ወጣቶቹ ከነበሩበት እኩይ ድርጊት በመውጣት የሰላም ጥሪውን ተቀብለው መመለሳቸው ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በመተከልና ካማሺ ዞኖች በተፈጠሩት የጸጥታ ችግሮች ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች መድረሳቸውን ጠቁመው፥ ተጨማሪ ጉዳት ሳይደርስ ያለፈውን ምዕራፍ በይቅርታና በጸጸት ዘግተን ወደልማት መመለስ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
አክለውም ከነበሩበት ድርጊታቸው ተጸጽተው በይቅርታ የሚመለሱ የጉሙዝ ወጣቶችን ወደልማት ለማስገባትና ተጠቃሚ ለማድረግም የክልሉ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን አስረድተዋል።
ወጣቶቹ ለ10 ቀን በሚቆየው ስልጠናቸውም፥ በሕገ መንግስት፣ ብዝሃነት፣ አብሮነትና አንድነት፣ በጉሙዝ ባህልና መልካም እሴቶች፣ በወንጀል ጉዳዮች እንዲሁም በሥራ ዕድል ፈጠራ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተሃድሶ ስልጠና እንደሚሰጣቸውም ተመላክቷል፡፡
የክልሉ መንግስት አሁንም ድረስ በጫካ ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች መሳሪያ አስረክበው እንዲመለሱ ተደጋጋሚ ጥሪ እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ ይህንን ዕድል ተጠቅመው ለሚመጡ ወጣቶች ስልጠና ወስደው ፍላጎታቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራ ማመላከታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡