ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በባህር ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል እንደምትሰራ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ኢንሼቲቭ የመሪነቱን ሚና ወስዳ በምስራቅ አፍሪካ በባህር ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል እንደምትሰራ ተገለፀ ፡፡
በዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም (ኢንተርፖል) አስተባባሪነት በምስራቅ አፍሪካ በባህር ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚያስችል ፕሮጀክት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱም÷ የቀይ ባህር ኢንሼቲቭ ፕሮጀክት ኃላፊዎች ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ስለ ፕሮጀክቱ ሁኔታ ገለፃ አድርገዋል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ፥ ለቀጠናው ብሎም ለዓለም ስጋት የሆኑ የወንጀል ዓይነቶችን ለመግታትና በትብብር ለመስራት የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎችን ለመግታት ትላልቅ ስራዎች መስራቷን ገልጸው÷ በ2015 ዓ.ም የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረትን በሊቀ መንበርነት በመረከብ የቀጠናው ሀገሮችን በማሳተፍ ወንጀሉን በጋራ ለመከላከል የሚጠበቅባትን ሚና ትወጣለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሽብርተኝነት፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም የጦር መሳሪያ ዝውውርን በመከላከል ሰፊ ተሞክሮ ያላት በመሆኗ÷ ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ያላትን ትልቅ ልምድ ለቀጠናው ብሎም ለአፍሪካ እንደምታካፍልም ነው የገለጹት፡፡
ሕገ ወጥ የሰዎችና የአደንዛዥ እፅ ዝውውርን እንዲሁም የተሰረቁና የጠፉ ሰነዶችን የመከላከል ዓላማ አድርጎ ለአምስት ዓመታት የሚቆየው ይህ ፕሮጀክት÷ በዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም አስተባባሪነት በዓለም አቀፍ ማሪታይም ድርጅት (አይ ኤም ኦ)፣ በአውሮፓ ሕብረት እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት መድሃኒትና ወንጀል ቁጥጥር በጋራ የሚሰራና በአፍሪካ ኢትየጵያን፣ ጂቡቲን፣ ሶማሊያን፣ ሱዳንን፣ የመንንና እና ኤርትራን በአባልነት ያቀፈ ነው፡፡
በማሪታይም ደህንነት ላይ ለተሰማሩና ለሕግ አስከባሪ ተቋማት የአቅም ግንባታ፣ የሎጀስቲክስ ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም ኦፕሬሽን ለማከናወን የኢትዮጵያ ሞጆ ደረቅ ወደብ ጣቢያ ፣ የሶማሊያ ቦሳሳ ወደብ፣ የሱዳን ፖርት ሱዳን፣ የየመን ኤደን ፖርት እንዲሁም ጅቡቲ ኢንተርናሽናል ፖርት የተመረጡ መሆኑ በውይይቱ ተገልጿል ፡፡
በፕሮጀክቱ መርሐ ግብር መሰረት ስልጠናው በሚቀጥሉት ቀናት በኢትዮጵያ ሞጆ ደረቅ ወደብ ጣቢያ ላይ ይጀመራል መባሉን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡