Fana: At a Speed of Life!

ቻይና በታይዋን ዙሪያ የውጊያ ዝግጁነት ቅኝት አደረገች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በታይዋን ዙሪያ የውጊያ ዝግጁነት ቅኝት ማድረጓን የሀገሪቱ ጦር አስታውቋል፡፡

የቻይና ጦር በዛሬው እለት እንዳስታወቀው ባለፉት ጥቂት ቀናት በባህር እና አየር  በአካባቢው  የውጊያ ዝግጁነት ቅኝት የተደረገ ሲሆን፥ በካባቢው ተፈጥሯል ላለው የአሜሪካ እና ታይዋን ጥምረት ምላሽ ለመስጠት ወሳኝ መሆኑን ነው ያመለከተው።

ታይዋን ግዛቷ እንደሆነች የምትገልፀው ቻይና በደሴቲቱ  ዙሪያ ያላት ወታደራዊ እንቅስቃሴ አጠናክራ ቀጥላለች ነው የተባለው።

ቻይና በተለይ አሜሪካ ለታይዋን በምታደርገው ድጋፍ ቅሬታ ውስጥ የገባች ሲሆን፥ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቤጂንግ ደሴቲቱን ካጠቃች ዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ ተሳትፎ ይኖራታል ማለታቸው ነው በዋናነት ቁጣውን የቀሰቀሰው።

ታይዋን የቻይና አካል መሆኗን የገለፀው  የቻይና ጦሩ፥ ወታደሮቹ የታይዋንን ነፃነት የሚደግፉ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትን ለማክሸፍ እና የአፀፋ ምላሽ ለመስጥት ዝግጅታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጿል።

ቀደም ሲልም ቻይና 30 የጦር አውሮፕላኖችን ወደ ታይዋን አየር  ክልል መላኳን የታይዋን  መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የታይዋን ወታደራዊ ባለስልጣናት ወታደራዊ እንቅስቃሴው ከፈረንጆቹ ጥር 23 ጀምሮ 39 የቻይና አውሮፕላኖች የታይዋንን የአየር ክልል  ጥሰው ገብተው እንደነበር አስታውሰው፥  ከሰሞኑ የተደረገው የቻይና የአውሮፕላን እንቅስቃሴ ቁጥር ግን ከወትሮው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ታይዋን በቻይና ውስጥ የምትገኝ ራስ ገዝ አስተዳደር ስትሆን ከ1949 ጀምሮ በቻይና የእርስ በርስ ጦርነት የተሸነፈው ወገን ወደ ደሴቷ በመሸሽ እንደመሰረታት ይነገራል፡፡

ምንጭ፦  ቢቢሲ እና ሮይተርስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.