ስፓርት

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ከእረፍት መልስ የፊታችን ሰኔ 7 ቀን ይጀመራል

By Mikias Ayele

June 01, 2022

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ከእረፍት መልስ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚጀምር የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የበላይነት የሚከናወነው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ውድድር ከ22ኛ ሳምንት ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ ሲከናወን መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅትን ተከትሎ ሊጉ ከግንቦት 15 ጀምሮ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡

በዚህም ሊጉ የፊታችን ሰኔ 7 ቀን 4 ሰዓት ሲዳማ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ በባህር ዳር ስታዲየም በሚያደርጉት ጨዋታ እንደሚመለስ አክሲዮን ማኅበሩ ይፋ አድርጓል።

ውድድሩም ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ነው አክሲዮን ማህበሩ ያስታወቀው፡፡

በተያያዘ ዜና ውድድሩ በሌላ ከተማ ይደረጋል በሚል የሚናፈሰው መረጃ የተሳሳተ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷ በዚህም ከ26ኛ እስከ 30ኛ ሳምንት ድረስ የሚደረጉ ጨዋታዎች በባህር ዳር ስታዲየም እንደሚቀጥሉ ተመላክቷል፡፡