Fana: At a Speed of Life!

የነዳጅ ድጎማ ማስተካከያው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫናን በማይፈጥር መልኩ እንደሚካሄድ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት የሚያደርገው የነዳጅ ድጎማ ማስተካከያ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫናን በማይፈጥር መልኩ እንደሚካሄድ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ።
መንግሥት በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚያደርገው ድጎማ ኢትዮጵያን ለ132 ቢሊየን ብር የእዳ ክምችት እንድትጋለጥ ማድረጉ ተገልጿል።
በባልሥልጣኑ የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ስታንዳርድ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ለገሰ ቱሉ÷ ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤቶቿ ሁሉ ነዳጅን በውጭ ምንዛሬ ግብይት እንደምትገዛ ገልጸዋል።
ነዳጁ አገር ውስጥ ከገባ በኋላም ከተገዛበት ዋጋ በግማሽ ባነሰ ገንዘብ ለግብይት እንደሚቀርብ ተናግረዋል።
ግብይቱም÷ መንግሥት በሚከተለው የድጎማ አሰራር መሰረት እንደ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ያሉ ጎረቤት አገራት ጋር ሲነፃጸር በግማሽ ያነሰና ሰፊ የዋጋ ልዩነት እንዲኖረው አድርጎታል ብለዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ለ132 ቢሊየን ብር የእዳ ክምችት እንድትዳረግ ማድረጉንና በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታስገባው ነዳጅ ወደ ጎረቤት አገራት በኮንትሮባንድ መልክ እንዲወጣ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ወደ ጎረቤት አገራት በኮንትሮባንድ መልክ የሚወጣው ነዳጅ÷ በአገር ውስጥ የነዳጅ ሥርጭት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቅሰው÷ ነዳጅ አቅራቢ ግለሰብና ድርጅቶችም የዋጋ ጭማሪ ወዳለበት አካባቢ በመሄድ የኮንትሮባንድ ንግዱ እንዲስፋፋ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የደቡብና ምስራቃዊ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ያለባቸው አካባቢዎች መሆናቸውንም በጥናት መረጋገጡን ነው የገለጹት፡፡
ጥናቱን መሰረት በማድረግም በቀጠናው ለሚገኙ ከተሞች የስርጭት ማስተካከያ ኮታ በማውጣት እንዲጠቀሙ ማድረግ የሚያስችል እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡
ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማስቆም ባይቻልም ከጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገው ድልድል 70 በመቶ የሚሆነውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ማስቆም እንደተቻለ ነው ያስረዱት፡፡
በዓለም አቀፉን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያትና መንግሥትም የዋጋ ማስተካከያ ሊያደርግ ይችላል በሚል ነዳጅን በማስቀመጥ እጥረት እንዲከሰት በሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
አገርን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ የሚገኘውን የነዳጅ ግብይት ወጥ ለማድረግም÷ መንግሥት የነዳጅ ግብይትና ሥርጭት ማስተካከያ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው÷ የዋጋ ማስተካከያውም ቀጣይ ሊመጣ የሚችለውን ችግር ታሳቢ በማድረግ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና በማይፈጥር መልኩ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ማስተካከያውም ልዩነቱን በአንድ ጊዜ ሕዝቡ ላይ በመጫን ሳይሆን ጫናውን ታሳቢ በማድረግ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅትና ግለሰቦችም የሚደረገው ድጎማ እንደሚቀጥል ጠቁመው÷ የድጎማ ተጠቃሚ የትራንስፖርት አግልግሎት ሰጪዎችም እስከ ስድስት ወራት ድረስ የዋጋ ጭማሪ እንደማያደርጉና በሂደት ከ10 እስከ 20 በመቶ በሚወሰን የታሪፍ ማሻሻያ እንዲወስዱ ይደረጋል ተብሏል።
የድጎማው አሰራርም ለጊዜው በደረሰኝ ሥርዓት የሚካሄድ ሲሆን÷ በቀጣይ ግን በኢትዮ-ቴሌኮም እና ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አማካይነት እየለማ በሚገኝ ቴክኖሎጂ ቁጥጥር እንደሚደረግበት ተጠቅሷል።
በሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይት ውስጥ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎችና ግለሰቦችን ተጠያቂ በማድረግ የሚወሰደው እርምጃም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በነዳጅ ሕገ ወጥ ግብይትን ለማስቆም ከጸጥታ አካላት ጋር ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረ ሲሆን÷ ህብረተሰቡም ሕገ ወጥ እንቅስቃሴን ሲያስተውል ጥቆማ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።
በ2014 በጀት ዓመት ብቻ 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ለነዳጅ ግዥ ወጪ የተደረገ ሲሆን÷ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በዚሁ ከቀጠለም በ2015 በጀት ዓመት 5 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ለጠቅላላ ነዳጅ ግዥ ልታወጣ እንደምትችል ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.