ሰላምን ለማደፍረስ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ መንግስት አስተማማኝ ቁመና እና ብቃት ላይ ይገኛል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰላምን ለማደፍረስ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ መንግስት አስተማማኝ ቁመና እና ብቃት ላይ እንደሚገኝ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አግልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ሰላምን ለማደፍረስ በሚንቀሳቀስ አካል ላይ እርምጃ ለመውሰድ መንግስት የተሟላ ቁመና እና ብቃት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
መንግስት በትላልቅ ከተሞች ከህብረተሰቡ ጋር በርካታ ውይይቶች ማድረጉን አውስተው÷ በውይይቶቹም በየአካባቢው የሚፈጸም የተደራጀ ዝርፊያ፣ ግድያ ፣ መፈናቀል እና ስጋት ህብረተሰቡን ከፍተኛ ስጋት ላይ እንደጣለው ሕዝቡ አንስቷል ብለዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች መንግስት በአፋጣኝ መቅረፍ እንዳለበት ህብረተሰቡ በአንድ ድምጽ ሊባል በሚችል መልኩ አጽንኦት ሰጥቶ መግለጹንም ነው ዶክተር ለገሰ የተናገሩት ፡፡
ሕግ የማስከበር ሥራው ከህብረተሰቡ የቀረበ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ለገሰ÷ ሥራውም ከፌደራል እስከ ክልል የተቀናጀ ሆኖ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሕግ የማስከበር እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ ነው ያነሱት፡፡
በዋነኛነት በኦሮሚያ ክልል አሸበሪው ሸኔን ማዕከል በማድረግ ከዚሁ ቡድን ጋር ትስስር ያለው የአልሸባብ የሽብር ቡድን እንደዚሁም ቀደም ብሎ ሽብርተኛው ህወሓት የፈጠራቸው ትስስሮች እና ኦሮሚያ በሚጎራበትባቸው የደቡብ፣ የሲዳማ እና የሶማሊያ አካባቢዎች ላይ ሕግ የማስከበር እርምጃው እየተወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ÷ በአዲስ አበባ ከተማ በጣም በከፍተኛ ደረጃ የተደራጀ፣ ለውንብድና የተሰለፈ እና ለዝርፊያ የተዘጋጀብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ሥራ ውስጥ የገባ ኃይል መኖሩን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
በአማራ ክልልም በተለያዩ አካባቢዎች በክልሉ ተከስቶ በነበረው እና የሽብር ቡድኑ ህወሓት በፈጠረው ጦርነት በተለያየ ምክንያት በነፍስ ግድያ ከእስር ቤት ያመለጡ፣ የመንግስትና የግለሰብን ሀብት ዘርፈው ፍርድ ቤት ውሳኔ የሰጠባቸው እንዲሁም በተለያየ የሽፍትነት ሥራ ላይ የተሰማሩ፥ ነገር ግን እራሳቸውን ፋኖ በሚል ስም በማደራጀት ከመንግስት የጸጥታ አካል ትይዩ የተደራጁ እና ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንቅፋት የሆኑ ኃይሎችን በመለየትና በእነዚህ ቡድኖች ላይ የሕግ ማስከበር ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዋነኛነት ቁልፍ አካባቢዎች ተብለው የተለዩ ቦታዎች ላይ በተወሰደ ሕጋዊ እርምጃ አካባቢዎቹ ነፃ መውጣታቸውንና ህዝቡም መደጋጋት መቻሉን ነው ዶክተር ለገሰ ቱሉ ከፋና ጋር በነበራቸው ቆይታ የጠቆሙት።
በዚህም ህብረተሰቡ በተጋጋ ሁኔታ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ተመልሶ ምርት ወደማምረት ተግባሩ እንዲገባ ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆናቸውን ጠቁመው÷ የምርት ግብዓቶች እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ሕግና ስርዓትን በማስከበር ህብረተሰቡን ወደ ምርት ተግባር የመመለስና የህብረተሰቡን አንገብጋቢ ችግሮች መፍታት የመጀመሪያውና ትልቁ የመንግስት ሥራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
“የእኛ መንግስት የሰላም፣ የዲሞክራሲ እና የልማት መንግስት ነው” ያሉት ዶክተር ለገሰ÷ ለእዚህም ሕግ ስርዓትን የማስከበር ሥራው ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን በአጽንኦት አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግስት፥ ኢትዮጵያን ከሚያፈርሱ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ከማይቀበሉ፣ ጽንፈኝነት እና አክራሪነት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲጎላ ከሚሰሩ ኃይሎች እንዲሁም ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን፣ ከማይሰብኩ ኃይሎች ጋር አብሮና ተባብሮ የማይሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ወንድማማችነት፣የሕዝቦች ብልጽግና እና ክብር ፣ የሀገር ሉዓላዊነት እና አንድነት በፍጹም ለድርድር የሚቀርቡ አይደሉም ነው ያሉት።
አሁን ባለንበት ሁኔታ የመንግስት አጠቃላይ የጸጥታ መዋቅር በውስጡ የሚታዩ ችግሮችን መቅረፍ ብቻ ሳይሆን÷ ከየትኛውም አካል የሚሰነዘር ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ የመቀልበስ የተሟላ ቁመና እና ብቃት አለው ብለዋል፡፡
“በዚህም ህብረተሰባችን ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ሊገባው አይገባም” ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አግልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ አስገንዝበዋል፡፡
ሙሉ ቃለ መጠይቁን ከቪዲዮው ይመልከቱ :-
https://www.youtube.com/watch?v=UERWCnrueWc
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!