አቶ ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ ኮንግረስ አባል ትሬንት ኬሊን ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ ኮንግረስ አባል ትሬንት ኬሊን ጋር ተወያዩ።
አቶ ደመቀ መኮንን ÷ በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ግጭት ለተጎዱ ወገኖች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂነትን እና የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በተወሰዱ እርምጃዎች ላይ ከኮንግረስ አባሉ ትሬንት ኬሊ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
የኮንግረስ አባል ትሬንት ኬሊ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ለግልፅነት አሰራር ዋጋ እንደምትሰጥ በመጠቆም፥ ኤች አር6600 እና ኤስ 3199ን እንደማይደግፉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርገውን ጥረት እንደሚከታተሉ እና ውሎ አድሮ ኢትዮጵያውያንን የሚጎዱ ረቂቅ ሕጎች እንደማይፀድቁ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በትግራይ ተፈጽሟል ለተባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ እና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በተወሰደው እርምጃ ላይ ባደረጉት ውይይት አቶ ደመቀ በመንግስት የተወሰዱ ተጨባጭ እርምጃዎችን አንስተዋል።
አቶ ደመቀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን፣ ከፍተኛ እስረኞች መፈታታቸውን፣ መንግስት በሀገሪቱ ውይይት እና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት።
ሆነኖም ህወሓት ለቀጣይ ዙር ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው፣ አሜሪካና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ህወሓት ፀረ-ሰላም ተግባራቱን እንዲተው ጫና እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈፃሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስት የነዳጅ አቅርቦትን ጨምሮ በትግራይ ለተጎዱ ወገኖች ሰብአዊ አቅርቦትን በማመቻቸት ከአጋሮች ጋር ለመተባበር የሰጠውን ትክክለኛ ምላሽ አድንቀዋል።
ስለ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አበረታች ስራዎች እና ስለቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት የተከበሩ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የሰላም ተነሳሽነት አድናቆታቸውን መግለጻቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡