ዴንማርክ የአውሮፓ ኅብረትን ጥምር መከላከያ ለመቀላቀል ወሰነች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዴንማርካውያን የአውሮፓ ኅብረቱን ጥምር የመከላከያ እና ደኅንነት ፖሊሲ ለመቀላቀል ወስነዋል፡፡
ትናንት በተካሄደው ህዝበ-ውሳኔ 67 በመቶ ያህል ዴንማርካውያን የአውሮፓ ኅብረቱን ጥምር የመከላከያ እና ደኅንነት ፖሊሲ ለመቀላቀል ድምጽ ሰጥተዋል፡፡
የህዝበ-ውሳኔውን መጠናቀቅ ተከትሎ የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜት ፍሬዴሪክሰን ለደጋፊዎቻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ÷ ዛሬ ዴንማርክ እጅግ ጠቃሚ የሆነ ውሳኔ አሳልፋለች ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል አብላጫውን ህዝበ ውሳኔ የተቃወሙ ዴንማርካውያን እንደሚሉት የተጓተተ ቢሮክራሲ በሚስተዋልበት የአውሮፓ ኅብረት ጥምር የመከላከያ እና ደኅንነት መዋቅር ውስጥ መግባት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያይላል፡፡
ምክንያቱም በቀጠናው ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የአውሮፓ ኅብረት በሚያካሂደው የዘመቻ ተልዕኮ የዴንማርክ ወታደራዊ ኃይል ተሳታፊ ከሆነ ዋጋ ሊያስከፍለው ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ሲ ጂ ቲ ኤን እና አር ቲ ኒውስ ዘግበዋል፡፡
ዴንማርክ በአውሮፓ ኅብረቱ ጥምር የመከላከያ እና ደኅንነት ኃይል ለመግባት ከመወሰኗ በፊት የኔቶ መሥራች አባል ሀገር መሆኗ ይታወሳል፡፡