በሰኔ ወር በተለያዩ ተፋሰሶች ላይ ጠንካራና እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ይስተዋላል – የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲቲዩት
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 204 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰኔ ወር በተለያዩ የሀገራችን ተፋሰሶች ላይ ጠንካራና እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ሊስተዋል እንደሚችል የሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲቲዩት አስታወቀ፡፡
በመጪው የሰኔ ወር እርጥበት ሰጪ የሚቲዮሮሎጂ ገጽታዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ተፋሰሶች ላይ አንጻራዊ ጥንካሬ እንደሚያሳዩ እና በተለይም በደቡብ ምዕራብ እና በመካከለኛው የሀገሪቱ ተፋሰሶች ላይ እርጥበት በመጠንም ሆነ በሥርጭት የተሻለ ሊሆን ይችላል ብሏል ኢንስቲቲዩቱ፡፡
ከሰኔ አጋማሽ በኋላም የእርጥበት መጠኑ ቀስ በቀስ ወደ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ ተፋሰሶች ላይ ሊስፋፋ እንደሚልችል እና በአንዳንድ ተፋሰሶች ላይም ከፍተኛ የእርጥበት መጠን እንደሚኖር ተመላክቷል፡፡
በዚሁ መሰረት በአብዛኛው ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊቤ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ አባይ፣ የመካከለኛውና የታችኛው ተከዜ፣ የላይኛው አዋሽ፣ የላይኛው ገናሌዳዋ እንዲሁም ዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች ከእርጥበታማ እስከ ከፍተኛ የእርጥበት መጠን የሚያገኙ ሲሆን፥ በጥቂት ተፋሰሶች ላይ ደግሞ በጣም ከፍተኛ የእርጥበት መጠን ሊኖራቸው እንደሚችል ከኢንስቲቲዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተጨማሪም ከፊል ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊቤ እንዲሁም የአባይ ተፋሰስ ምዕራባዊ አጋማሽ ተፋሰሶች ላይ ከከፍተኛ እስከ በጣም ከፍተኛ የእርጥበት መጠን ጠንካራ የደመና ክምችቶች እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡
የታችኛው ገናሌዳዋ፣ የመካከለኛው አዋሽ እና የላይኛውና የመካከላኛው ዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች በጥቂት ቦታዎቻቸው ላይ አነስተኛ የእርጥበት መጠን እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡