አዲስ ወግ የውይይት መድረክ ተካሄደ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 27 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የሚዘጋጀው አዲስ ወግ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
መድረኩ “የሎጅስቲክስ ዘርፍ ሪፎርም” በሚል ርዕሰ የተካሄደ ሲሆን፥ በመድረኩ ላይ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የግሉን ዘርፍ ዕድገት ለማበረታታት እና ማነቆዎችን ለማስወገድ መንግሥት ብሔራዊ የሎጂስቲክ ስትራቴጂ ነድፎ እየተሠራበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት ቺፍ ኤክስኪውቲቭ ኦፊሰር አቶ ሮባ መገርሳ በበኩላቸው፥ የግሉን ዘርፍ አስተዋጽኦ ለማሳደግ መንግሥት ዕሴትን ለመጨመር ማድረግ ያለበት ድጋፍ መለየቱን ገልጸዋል።
ለዚህም በደረቅ ወደቦች ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከቴክኖሎጂ አንጻርም የአንድ መስኮት አገልግሎት የስራውን ሂደት እያቀላጠፈው ነው ብለዋል።
አያይዘውም የግሉ ዘርፍ እና የባለድርሻ አካላት ሚና እንዲሁም ፋይናንስ ለዘርፉ እድገት ያለው አስተዋጽኦ ላይ ማተኮር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
የሎጂስቲክስ ማኅበረሰብ ፕሬዚዳንት የሆኑት ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ጌታሁን ደግሞ፥ በሀገር ደረጃ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የሚያስተሳስር የሎጂስቲክስ ስርዓት አለመዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
የሎጂስቲክስ ምክር ቤት መቋቋም ይህንን እውን ለማድረግ ያግዛል ያሉት ወይዘሮ ኤልሳቤጥ፥ የሎጂስቲክስ ዘርፍን ስናስብ የጊዜና የገንዘብ ዋጋን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብንም ብለዋል።
እየተተገበሩ ካሉት ማሻሻያዎች ባለፈም ቀጣይ እርምጃዎችን ማፋጠን ይገባልም ነው ያሉት፤ የሎጂስቲክስ ልማት ቁልፍ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ መሆኑን በመጥቀስ።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመድረኩ የተሳተፉት ዶክተር ማቴዎስ ኢንሰርሙ፥ የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ ለምሥራቅ አፍሪካ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን አውስተዋል።
ይሁን እንጅ በዕሴት ላይ ዋጋ አለመጨመሩ እና ሥራው ያለቀለት ምርት ማስገባቱ አሉታዊ ጎን እንዳለው አንስተዋል።
ከዓለም አቀፍ አካሄድ አንጻር ተለዋዋጭና አዳጊ ፍላጎት መኖሩ፣ የተወሳሰበ የንግድ ስርዓት፣ የወጪ ጫና፣ ዓለም አቀፋዊነት አመጣሽ ተጋላጭነት፣ የዘለቄታዊነት ሚና፣ የሎጂስቲክስ ክህሎት፣ ቴክኖሎጂ፣ ስታንዳርዳይዜሽን፣ የሀገራት ስምምነት እና መሰል ሁኔታዎች በዘርፉ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩም አስረድተዋል።
የሎጂስቲክ ዘርፍ ከፍተኛ መሻሻል እንዲታይበትም ሥራዎች በአፋጣኝ ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ እንዳሉትም፥ የሎጂስቲክስ ሥርዓቱ ለእድገት አጋዥ ከመሆን ይልቅ አደናቃፊ መሆኑ ታይቶ ስርዓት ተኮር ማሻሻያ ተጀምሯል።
ማነቆዎችን ከእነመንስኤያቸው መለየት፣ የመፍትሔ ሀሳቦችን ወደ መርሀግብር ለውጦ መተግበር እንዲሁም ወደ አንድ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲያድግ የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውንም አስታውሰዋል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision