Fana: At a Speed of Life!

12ኛው የኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሳተፉበት 12ኛው የኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ተከፈተ።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በጋራ ያዘጋጁት የንግድ ትርኢት በአዲስ አበባ ኤግዚቪሽን እና ገበያ ልማት ማዕከል ነው በይፋ የተከፈተው፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው ተገኝተዋል፡፡

በዚህ ወቅት የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ፥ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ተልዕኮውን ለመወጣት መንግስታዊ ከሆኑና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር እንደሚሠራ ገልፀዋል።

የንግድ ትርኢቱ ጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማት ልምድ የሚያገኙበት መሆኑን ጠቁመው፥ ከተለያዩ ክልሎችና ከተሞች ዕድሉን አግኝተው የተሳተፉት ኢንተርፕራይዞችም ይህንን ዕድል በዘላቂነት ንግድና አገልግሎታቸውን ለማሳደግ እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል።

“የኢትዮጵያን ይግዙ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የንግድ ትርኢት ላይ ከ250 በላይ የሚሆኑ አምራች ኢንተርፕራይዞችና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የሚሳተፋ ሲሆን ፥ ከእነዚህ መካከልም በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ድጋፍ የሚደረግላቸው ከ60 በላይ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች መሳተፋቸው ተገልጿል።

ለአምስት ቀናት የሚቆየው ዓለም ዓቀፍ የንግድ ትርዒት አካል የሆነው ከ50 በላይ ከንቲባዎች የተሳተፉበት የግሉ ዘርፍና ከንቲባዎች ምክክር መድረክ እየተካሄደ ሲሆን ፥ በንግድ ትርኢቱ ምርቶች እና አገልግሎቶች ቀርበዋል።

በተጨማሪም የንግድ ትርኢቱ አካል የሆኑት መድረኮች የአቻ ለአቻ የንግድ ፣ የፓናል ውይይት፣ ስራና ሰራተኞች የሚገናኙበት እንደሆነም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

12ኛው የኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ለተሳታፊዎች የገበያ ትስስር፣ የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ጥምረትና በአገር ውስጥና በውጪ አምራቾች አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች መካከል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ታምኖበታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.