በሐረሪ በቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሐብቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል – አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 25 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልላዊ መንግስት በቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሐብቶችና ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡
በሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የተመራው የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ልዑካን ቡድን በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ ተገኝቶ ከከተማ ጽዳት ፣ ከደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ እና አያያዝ እንዲሁም ከመሠረተ ልማትና ከአረንጓዴ ልማት ጋር በተያያዘ በቱርክ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎችን እየጎበኘ ይገኛል።
ልዑኩ በኢስታንቡል ከሚገኙ የተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ቱርክና ኢትዮጵያ የቆየ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አንስተዋል።
ቱርክ በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማትና የሰብዓዊ ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኗንም አመላክተዋል።
ርዕሰ-መሥተዳድሩ የቱርክ አምባሳደሮች እና ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ ጊዜያት በሐረሪ ክልል ጉብኝት ማድረጋቸዉን አስታውሰው ÷ በትምህርት፣ በጤና፣ በሰብዓዊ እና ማኅበራዊ ልማት እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፎች ላይ ድጋፍ በማድረግም የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት በተግባር አሳይተዋል ብለዋል፡፡
የሐረሪ ክልል በቱሪዝም ዘርፍ ዕምቅ ሐብት እንዳለው ገልጸው በዘርፉ ለሚሠማሩ ቱርካውያን ባለሐብቶች እና ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።
በጉብኝት መርሃ-ግብሩ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ጨምሮ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።’