በአማራና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የወባ በሸታ ስርጭት እየጨመረ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል እና ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የወባ በሸታ ስርጭት እየጨመረ መሆኑ ተገልጿል።
በአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ቡድን መሪ አቶ ዳምጤ ላንክር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ አሁን ላይ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖች የወባ በሽታ ተከስቷል።
በክልሉ በአንድ ሳምንት ብቻ ከ 11 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን ጠቁመው ÷ባለፉት 9 ወራት በክልሉ ወደ ግማሽ ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን አስታውሰዋል፡፡
የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የፕሮግራሞች ዘርፍና ምክትል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሀይሉ ዘውዴ በበኩላቸው ÷ በክልሉ በወባ በሽታ የመያዝ ምጣኔ 69 በመቶ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
የስርጭት ምጣኔው ደግሞ 54 በመቶ ላይ መድረሱን ነው ምክትል ቢሮ ሃላፊው ያመላከቱት።
በሁለቱም ክልሎች እየጨመረ ለመጣው እና ያለጊዜው ለተከሰተው የወባ በሽታ መንስኤው የዝናብ እጥረት መሆኑን ሀላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
ህብረተሰቡ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ ግብዓቶች ላይ ያለው የአጠቃቀም ጉድለትን የሚያነሱት ሃላፊዎቹ÷ በሽታውን መከላከል የሚያስችሉ የግብዓት እጥረቶች በወቅቱ አለመድረሳቸውም ለበሽታው ስርጭት መስፋፋት ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሎቹ ያለውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመግታት የአጎበር ስርጭት እና የኬሚካል ርጭት በሽታው አሳሳቢ በሆነባቸው አካባቢዎች ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
በዙፋን ካሳሁን
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!