የቡሬ የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት እጥረት እንደገጠመው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቡሬ የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት እጥረት እንደገጠመው የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ ጣምአለው በሰጡት መግለጫ÷ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ለመግባት የኃይል አቅርቦት ችግር እንቅፋት እንደሆነበት ተናግረዋል ።
ችግሩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአማራ ክልል የኃይል አቅርቦት ቋት ለመገንባት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር ያደረገውን ስምምነት ባለመተግበሩ የተከሰተ መሆኑንም ሃላፊው አብራርተዋል ።
ፓርኩ 100 ፕሮጀክቶችን ይይዛል ተብሎ ቢጠበቅም ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከደብረማርቆስ ቡሬ ለመገንባት የተስማማውን የኃይል አቅርቦት ቋት ባለመገንባቱ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል ነው ያሉት ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በክልሉ የኃይል አቅርቦት ቋቱን ግንባታ ለማከናወን ውል የፈፀሙ የህንድና የቻይና ኩባንያዎችን የቅርብ አመራርና ክትትል ባለማድረጋቸው የተፈጠረ ችግር ስለመሆኑም አቶ ብርሀኑ አስረድተዋል፡፡
ኢንዱስትሪ ፓርኩ ባለፈው መጋቢት ወር ወደ ስራ ቢገባም በስራ ላይ ያለ አንድ ፋብሪካ ፣ በግንባታና ማሽን ተከላ ሂደት ላይ ያሉ ሁለት ፋብሪካዎች እና በቅድመ ግንባታ ሂደት ላይ ያሉ 18 ኩባንያዎች የኃይል አቅርቦት እጥረቱ እንቅፋት እንደሆነባቸው አብራርተዋል ።
ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ በጥቂቱ 4 ሺህ 800 ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ መሆኑን ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡
ፓርኩ ያለውን ምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳ በመገንዘብ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአፋጣኝ የኃይል አቅርቦት ስራውን እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።
በበርናባስ ተስፋዬ