በደብረ ብርሀን ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ተስፋ ብርሃን ህጻናትና ቤተሰብ ልማት ድርጅትና ቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ ከሌጎ ፋውንዴሽን ባገኙት የገንዘብ ድጋፍ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የተስፋ ብርሃን ህጻናትና ቤተሰብ ልማት ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ተረፈ ሲሳይ እንዳሉት፥ የተደረገው ድጋፍ የዳቦ ዱቄት፣ ዘይት፣ ሳሙናን የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ነው፡፡
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ድጋፍ የሚያደርገው ተስፋ ብርሃን ህጻናትና ቤተሰብ ልማት ድርጅት በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ስራ እስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፀጋዬ በየነ ለድጋፉ አመስግነው፥ መሰል ድጋፎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል ፡፡
ድጋፍ የተደረገላቸው ተፈናቃይ ወገኖችም ለተደረገላቸው ድጋፍ ያመሰገኑ ሲሆን ፥ ሌሎች አጋር አካላቶችም እንዲጎበኟቸው ጠይቀዋል፡፡
በአይናለም ስለሺ