“የህዝብን አንገብጋቢ ጉዳዮችና እና መሰረታዊ ጥያቄዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይገባል” – ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ የአንገረብ ግድብን ጎብኝተዋል፡፡
ከዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በተጨማሪ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ፣ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሞላ መልካሙ እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በጉብኝቱ ተሳትፈዋል፡፡
በዚህ ወቅት ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፥ ብልጽግና ፓርቲ በአንደኛዉ የፓርቲ ጉባዔ ወቅት በዋነኛነት አቅጣጫ ሰጥቶ ካለፈባቸዉ ጉዳዮች መካከል የህዝብን አንገብጋቤ ጉዳዮችና እና መሰረታዊ ጥያቄዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ ምላሽ መስጠት መሆኑን በማስታወስ በአሁኑ ወቅት በአንገረብ ግድብ ላይ የተጋረጠዉ የህልዉና አደጋና በጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ላይ የተፈጠረዉ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ችግር ፓርቲዉ ባስቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት በፍጥነት እልባት ሊሰጠዉ እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ በበኩላቸዉ÷ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች መሰረታዊ ጥያቄ የሆነዉ ይህ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ችግር ምላሽ እንዲያገኝ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደስራ ሊገቡ እንደሚገባ ተናግረዋል ፡፡
ለጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ከሚቀርበዉ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው ከዚሁ ግድብ መሆኑን በማንሳት የዚህን ግድብ ህልዉና ማስጠበቅና ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡
የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው ÷ሌሎች አማራጮችን በተለይም የመገጭ እና የጣና ዉሃ ሃብትን ለመጠቀም በርካታ ተግባራዊ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ከ700 ሺህ ህዝብ በላይ ለሚኖርባት ጎንደር ከተማ በቀን 60 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ዉሃ የሚያስፈልግ ሲሆን ÷በአሁኑ ወቅት በግድቡ ላይ በደለል አማካኝነት በተጋረጠዉ ችግር ለነዋሪዎቿ እየቀረበ የሚገኘዉ በቀን ከ 14ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ዉሃ ያነሰ መሆኑ ታዉቋል፡፡