የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሴት ሰራተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፉን በጅማ ከፈተ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሴት ሰራተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፉን በጅማ ከተማ አስመርቆ ስራ አስጀመረ።
የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነቱን የተሻለ ለማድረግ በሴቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጠውን ቅርንጫፍ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የጅማ እና የአከባቢው ቆንጆ በነበረችው በታሪካዊቷ እንስት ቢሊሌ ወይም ማህቡባ ስም ተሰየመ ነው።
ቅርንጫፉን መርቀው ስራ ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጅማ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ መልካሙ ዴሲሳ፥ ቅርንጫፉ በሀገር አቀፍ በሴት የሚመራ ሁለተኛው ቅርንጫፍ መሆኑን ገልጸዋል ።
በተጨማሪም ሴቶችን ወደ አመራርነት በማምጣትና አገልግሎቱን የበለጠ የተሳለጠ ለማድረግ ታስቦ የተከፈተ መሆኑንም ተናግረዋል።
በጅማ ከተማ 17ኛ ቅርንጫፍ ሲሆን ፥ በከተማው በሴቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ብቸኛው ባንክ እንደሆነም ነው የተነገረው።
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የባንኩ ደንበኞች፣ ሰራተኞችና ከጅማ ከተማ ሴቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በወርቃአፈራሁ ያለው