በሩሲያ ላይ የተጣለው የነዳጅ ዘይት ማዕቀብ በአውሮፓ ህብረት እና ሩሲያ ላይ ተጨማሪ ችግር እንደሚፈጥር ተንታኞች አስጠነቀቁ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 27 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ የጣለው የነዳጅ ዘይት ማዕቀብ ተጨማሪ ችግር እንደሚፈጥር ተንታኞች አስጠነቀቁ።
መቀመጫውን ቤልጂየም ብራሰልስ ያደረገው የባለሙያዎች ቡድን አሁን ላይ ህብረቱ የጣለው የነዳጅ ዘይት ማዕቀብ ለሩሲያም ሆነ ለአውሮፓ ሃገራት ተጨማሪ ችግር ያስከትላል ሲል አስጠንቅቋል።
አሁን በአውሮፓ ሃገራት የተከሰተው የዋጋ ንረት በዚህ ሳቢያ እንደሚያሻቅብም አስጠንቅቋል።
ይህም ለአውሮፓ ሃገራት ከዓለም ሁሉ የከፋው ይሆናልም ነው ያሉት የብሩገል የአጥኚዎች ቡድን ሃላፊ ገንትራም ወልፍ።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በአውሮፓ የንግድ እንቅስቃሴና ደንበኞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል ያሉት ሃላፊው፥ ሁኔታው በሃገራቱ በሚታይ መልኩ የመግዛት አቅምን ያሳጣል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።
ይህ መሆኑ ደግሞ መንግስታት የነዳጅ ድጎማ እና ግብር ቅነሳ ብሎም ለዜጎች የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ በማስገደድ የእዳ ጫና ውስጥ ይከታቸዋል ሲሉም ይገልጻሉ።
ማዕቀቡ በአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ላይ ጫናውን ያሳድራል የሚሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው፥ ባንኩ የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር የወለድ ምጣኔን እንዲያሳድግ እንደሚያስገድደውም አስረድተዋል።
ማዕቀቡ ከህብረቱ አባል ሃገራት ባለፈም በሩሲያ ላይ የረጅም ጊዜ ጉዳት ያስከትላልም ነው ያሉት።
ለዚህም ሩሲያ ከነዳጅ ዘይት የምታገኘውን ገቢ በመቀነስ አመታዊ የነዳጅ ትርፏን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳጣት ያስረዳሉ።
ባለሙያዎቹ ማዕቀቡ ችግሮችን ከማባባሱ አስቀድሞ ግን ሃገራቱ አሁንም ቆም ብለው በማሰብ መፍትሄ ማበጀት ይችላሉ ባይ ናቸው።
የአውሮፓ ህብረት ከዩክሬን ሩሲያ ግጭት ጋር በተያያዝ ስድስተኛውን ማዕቀብ በሩሲያ ላይ መጣሉ የሚታወስ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የህብረቱ አባል ሃገራት ከሩሲያ የሚገዙትን ነዳጅ ለማቆም የስድስት ወር ጊዜ እንደተሰጣቸው የአር ቲ ዘገባ ያመላክታል።