በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሰላም ጥሪ የተቀበሉና ስልጠና የወሰዱ ኃይሎች በልማት ስራ ላይ መሰማራታቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉና ስልጠና የወሰዱ ኃይሎች በተለያየ የልማት ስራ ላይ መሰማራት መጀመራቸውን የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ ገልፀዋል።
ፅንፈኛ አመለካከት ይዘው ሲዋጉ የነበሩት ታጣቂ ኃይሎች በመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስትና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባከናወኑት የፀጥታ ስራ አብዛኞቹ የመንግስትን ጥሪ የተቀበሉና ስልጠና የወሰዱ አባላት በእርሻ፣ በማዕድን ዘርፍና ቀደም ሲል በነበሩበት የስራ መስክ ላይ መሰማራታቸው ነው የተገለጸው።
ከአራትና አምስት ወራት በፊት የነበረውን የፀጥታ ችግር በመቅረፍ አሁን ላይ የመተከል ዞን ፊቷን ወደልማት ማዞር ጀምራለች ያሉት አስተዳዳሪው፥ በእርሻ ስራ ለመሰማራት ለተደራጁ አባላት በቅድሚያ 6 የእርሻ ትራክተሮች መንግስት 30 ከመቶ ቅድመ ክፍያን በመሸፈን ለርክክብ ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል።
ትራክተሮቹ በሁሉም የመተከል ዞን ወረዳዎች የሚታደሉ ሲሆን ፥ 11ተጨማሪ ትራክተሮችም በግዢ ሒደት ላይ እንዳሉም ገልፀዋል።
የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱት ተመላሽ ታጣቂዎች መካከል 17 በማዕድን ስራ፣ 92 በንግድ ስራና ወደነበሩበት የመንግስት ስራ የተመለሱ 43 እንዲሁም 493 አባላት ደግሞ በፀጥታ ስራ ላይ ተሰማርተዋል ነው ያሉት።
ወደ ፀጥታ ስራ እየተሰማሩ ላሉት በቂ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት የዳንጉር ወረዳ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሻለቃ ደምስ ዳኜ ናቸው።
አሁን ላይ የፀጥታ ስራው በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ጭምር እየተከናወነ በመሆኑ ዜጎችን ወደቀያቸው የመመለስ ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!