Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ዜጎች የሚፈልጉትን መረጃ የማግኘት መብታቸው እንዲከበር እየሰራ እንደሆነ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ዜጎች የሚፈልጉትን መረጃ በነጻነት የማግኘት መብታቸው እንዲከበር እየሰራ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነጻነት ህግ አፈጻጸምን አስመልክቶ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትና ከመገናኛ ብዙሃን ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በዚሁ ወቅት እንዳነሱት ፥ በመንግስት አገልግሎቶችና ፕሮግራሞች ዙሪያ ዜጎች የሚፈልጉትን መረጃ በነጻነት የማግኘት መብት አላቸው።

በወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና አገራዊ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ዙሪያ የተደራጀና የተተነተነ መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው በህገ- መንግስቱ የተቀመጠ ስለመሆኑ አመላክተዋል።

ሆኖም በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የመረጃ ነጻነት ጉዳይ በሚገባው ልክ ያልተሰራበት መሆኑን ጠቅሰው ፥ ይህንን ለማስተካከል መንግስት በየደረጃው ካሉ የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ መዋቅሮች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የዜጎች መረጃ የማግኘት ነጻነት መከበሩ ከለውጡ ማግስት አንስቶ ለፕሬስ ነጻነት የተከፈተውን አዲስ ምዕራፍ የማገዝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ሆኖም ግን በመረጃ ነጻነት ስም የሚካሄዱ ግጭት ቀስቃሽና አገር አፍራሽ የሆኑ የትኛውም ዓይነት የመረጃ ስርጭት በሚያወጡት ላይ ህግ የማስከበር ስራ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ የህዝቡ የመረጃ ነጻነት የተጠበቀ እንዲሆን የቁጥጥርና ክትትል ሂደቱን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ በበኩላቸው ፥ እስካሁን የመረጃ ነጻነት ህጉ በሚጠበቀው ልክ ያልተተገበረው በሚፈለገው ልክ በቅንጅት መስራት ባለመቻሉ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ተቋሙ ችግሩን ለመቅረፍ በየጊዜው ከመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ዘርፉ ጋር ምክክር ሲያደርግ የየራሳቸውን ችግሮች ሲያነሱ የቆዩ ሲሆን ፥ ይህ መድረክ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ጭምር የሚረዳ ይሆናል ብለዋል።

በመድረኩ የግልና የመንግስት ሚዲያ ተቋማትን በመወከል የተገኙ የስራ ሃላፊዎች በሰጡት ሃሳብ ፥ በኢትዮጵያ የመረጃ ነጻነት እንዲሰፍን ሁሉም የሚዲያ ተቋማት የሚሳተፉበት አሰራር ሊተገበር እንደሚገባው ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.