የመንግስት ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎችን ለማሳካት በትኩረት መስራት ይገባል – አቶ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 27 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የሕግ የበላይነትን በማስከበር የመንግስትን ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎችን ለማሳካት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።
አፈ ጉባኤው በአርባ ምንጭ በመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ ዙሪያ ለብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ሲሰጥ በቆየው ስልጠና ማጠቃለያ ላይ ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ ኩሩ ህዝብና አኩሪ ታሪክ ያላት እንዲሁም በተፈጥሮ ፀጋ የበለፀገች ብትሆንም የተሰጠንን ፀጋ ባለመጠቀማችን በተፈለገው ልክ ሳናድግ ቆይተናል ብለዋል።
ባለፉት አመታት የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ መዳከም፣ የአመራሩ እርስ በእርስ መሳሳብና መጓተት፣ በሀገሪቱ ፀረ ዴሞክራሲነት እና አምባገነንነት እንዲስፋፋ፣ በተግባር አፈፃፀም ውጤታማነት እንዳይኖር ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በቀጣይ የብልፅግና ፓርቲ አመራር በቅንጅት የህግ የበላይነትን በማክበር እና በማስከበር ሰላም በማረጋገጥ፣ ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር እና የመንግስት ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎችን ለማሳካት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም አንስተዋል።
በተለያዩ ስልጠናዎች የሚገኙ እውቀቶችን ወደ ተግባር ቀይሮ ውጤት ከማስመዝገብ አንጻር ክፍተት መኖሩን ጠቁመው፥ አመራሮች በስልጠና ያገኙትን የአመለካትና የአስተሳሰብ አንድነት ወደ ተግባር በመቀየር ለህዝባቸው ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ሠላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሃዊ እና በህዝቡ ዘንድ ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አመራሩ የድርሻቸውን ሊወጣ ይገባል ማለታቸውንም ከጋሞ ዞን አስተዳደር ህዝብ ግንኙነት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision