በጋምቤላ በክረምቱ የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰት የመከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ተባለ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 29 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው ክረምት የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወንድማገኝ በላይነህ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የወባ በሽታ ጉዳት እንዳያደርስ ከ114 ሺህ በሚበልጡ ቤቶች የወባ በሽታ አምጪ ትንኝ መራቢያ እንዳይሆኑ የኬሚካል ርጭት በመካሄድ ላይ ይገኛል ።
ክልሉ የወባ ወረርሽኝ ከሚከሰትባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ በመሆኑ ከክረምቱ ጋር ተያይዞ ወረርሽኝ እንዳይከሰት የመከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበርን በአግባቡ በመጠቀምና ውሃ የሚያቁሩ ቦታዎችን በመድፈንና በማጽዳት በሽታው እንዳይከሰት እየተከላከለ መሆኑን ጠቁመዋል።
በበሽታው ተይዘው ወደ ህክምና ተቋም የሚሄዱ ሰዎች የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙም በጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦት እንዲሟላ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በተደረገው የቅድመ መከላከል ስራም ከ450 ሺህ በላይ ህዝብ ከበሽታው ይጠበቃል ተብሎ እንደሚገመት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የጋምቤላ ክልል የወባ በሽታ ጥቃት ከሚያደርስባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል።