ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክ/ ከተማ አዲስ የንግድ እና የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ አስጀመሩ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ አዲስ የንግድ እና የመኖሪያ ቤቶች ግንባታን በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል፡፡
ከንቲባዋ አጠቃላይ 36 ቤቶች ግንባታ ያስጀመሩ ሲሆን÷ ከእነዚህም ውስጥ 28 የንግድ ቤቶች እና 8 መኖሪያ ቤቶች ይገኙበታል።
የሚገነቡ ሱቆቹና የመኖሪያ ቤቶች ወጣቶችንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሏል።
ግንባታው በአንድ ወር እንደሚጠናቀቅ እና ወጪውም በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እንደሚሸፈን ተጠቅሷል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የምንሰራቸውን የልማት ስራዎች አጠናክረን እንቀጥላለን፤ለሚሰሩ የልማት ስራዎች የባለሀብቶች ተሳትፎ የላቀ ነው ማለታቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
“ሁላችንም ዜጎች ተባብረን ለአንድ አላማ ከሰራን ሀገሪቱ የማትለወጥበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ግንባታው ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግበት የተገለጸ ሲሆን÷ ቤቶቹ ሲጠናቀቁ አቅም ለሌላቸው ወገኖች እንደሚተላለፉ ታውቋል፡፡