Fana: At a Speed of Life!

ለትግራይ ክልል ከባለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብርና 87 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ ተልኳል- የጠቅላይሚኒስትር ጽህፈት ቤት

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለትግራይ ክልል ከባለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ጥሬ ብር፣ 87 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ እና ከ783 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ መላኩን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ትናንት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለውጭ ጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማበራሪያቸውም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተያይዞ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚደረገው የሰብዓዊ እርዳታ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡
በዚህ መሰረትም በፈረንጆቹ 2021 ሐምሌ ወር ጀምሮ እስከ 2022 ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ጥሬ ብር ወደ ትግራይ ክልል መላኩን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም 87 ሺህ ሜትሪክ ቶን የሰብዓዊ እርዳታ ምግብ እና ከ783 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ መላኩን ነው ያብራሩት።
በሌላ በኩል በተጠቀሱት ጊዜያት 217 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የህክምና መድሃኒቶች እንዲሁም የመጠለያ ግብዓቶች ጨምሮ 130 ሺህ ኪሎ ግራም ምግብ ነክ ያልሆኑ የሰብዓዊ ድጋፎች መላካቸውን ጠቁመዋል፡፡
ነገር ግን ህወሓት ቀጣይ የዝናብ ወቅት እየመጣ ባለበት በዚህ ወቅት ለሌላ ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን በመጠቆም፥ ህዝቡን በሃይል ለጦርነት እየመለመለ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ይህ የህወሓት አረመኔያዊ ድርጊት ቀጣዩን የእርሻ ስራ እንደሚያደናቅፍ እና በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ እንደሚያባብስ አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል እስካሁን በአፋር ክልል በግጭቱ ጉዳት ለደረሳበቸው ዜጎች 19 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ መከፋፈሉን የገለጹት ብለኔ ስዩም፥ለአማራ ክልል ተፈናቃዮችም 244 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡
ከጠቅለይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕድ የናጄሪያ ጉብኝት ጋር በተያያዘም ሲያብራሩ፥ በቆታቸው ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት መሃመዱ ቡሃሪ ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረጉ የሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል፡፡
አገራቱ በቀጣይ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያለቸውን ትብብር አጠናክረው መቀጠል በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ በትኩረት መወያየታቸውንም ጠቁመዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.