Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ከባሕሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የተመራ የልዑካን ቡድን ከባሕሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሼኻ ራና ቢንት ኢሳ አል ኻሊፋ ጋር ተወያየ።

በውይይታቸውም አምባሳደር ብርቱካን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዱባይ እና በአቡዳቢ ከተሞች ከመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ባካሄዱት ውይይት በተለይም ከባሕሬን ለመጡ ዜጎቻችን ቃል በገቡት መሰረት በባሕሬን ማናማ የቆንስላ ጄኔራል ፅህፈት ቤት የሚከፈትበትንና ውሳኔው የሚፈጸምበትን ሁኔታ የባሕሬን መንግሥት እንዲያመቻች ጠይቀዋል።

በሀገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎቻችን የመኖሪያና የስራ ፍቃድ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች እንዲሁም ከባሕሬን ጋር ለመፈራረም የተጀመረው የሠራተኛ ስምሪት የመግባቢያ ሰነድ ፈጥኖ የሚጠናቀቅበትንና የሚፈጸምበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹም ነው የጠየቁት።

የባህሬን መንግስት ለኢትዮጵያ ዜጎች መብትና ክብር መጠበቅ እያደረገ ያለውን ጥረት አመስግነው፥ በባሕሬን ማናማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ እያላቸው የታሰሩ ዜጎችን ጉዳይ ታይቶ አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባም አንስተዋል።

በተጨማሪም ባባሕሬን ያሉ በኢትዮጵያውያን የተመሰረቱ የእምነነት ተቋማት በሀገሪቱ ህግ ተመዝግበው እውቅና እንዲሰጣቸውና የተሻሉ የማምለኪያ ቦታዎች እንዲያገኙ፣ በባሕሬን ያሉ ኢትዮጵያውያን ህጻናት የሚማሩበት የማህበረሰብ ትምህርት ቤት እንዲከፈት እና አደረጃጀቶች እውቅና እንዲያገኙ ጠይቀዋል።

የባሕሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሼኻ ራና ቢንት ኢሳ አልኻሊፋ ለተነሱ ጥያቄዎች ትኩረት ሰጥተው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

ከአሁን በፊት በባሕሬን በኩል ከኢትዮጵያ ጋር ለዲፕሎማሲው ማህበረሰብ የቪዛ ማስቀረት ስምምነት ለመፈራረም የቀረበው ጥያቄ ውሳኔው እንዲፋጠንና ባሕሬንን ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም የማስተሳሰር ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል።

በባሕሬንና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ በመወያየት የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.