የሀገር ውስጥ ዜና

በዋግኽምራ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የአልሚ ምግብ ድጋፍ ተደረገ

By Meseret Awoke

June 07, 2022

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች አስተዳደር በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉ ወገኖች 6 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የአልሚ ምግብ ድጋፍ አደረገ፡፡

የልማት ድርጅቱ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው ጌቴ እንዳሉት ፥ የልማት ድርጅቱ በክልሉ ከሚሰራው የልማት ስራዎች ጎን ለጎን የማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

የልማት ድርጅቱ ቀደም ሲል በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት በዋግኽምራና ሰሜን ወሎ ዞኖች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 6 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አድርጓል።

በዛሬው ዕለትም በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው 500 ኩንታል የአልሚ ምግብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ተመሳሳይ መጠን ያለው ድጋፍም በሰሜን ወሎ ዞኖች ለሚገኙ ተፈናቃዮች መላኩንም ነው ያመላከቱት።

ከድጋፉ ውስጥም 100 ኩንታል ፋፋ፣ 150 ኩንታል ማካሮኒ፣ 200 ኩንታል ፉርኖ ዱቄት እና 5 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት ይገኝበታል።

አስተዳደሩም ከልማት ስራዎች ጎን ለጎን የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰው እስኪቋቋሙ የሚያደርገውን የሰብዓዊ ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የብሄረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስቡህ ገበያው በበኩላቸው ፥ የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ያደረጉት ድጋፍ የወገንተኝነት ማሳያ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረጉ ድጋፍ በተቀዛቀዘበት ወቅት የተደረገ ድጋፍ የተፈናቃይ ወገኖችን ወቅታዊ የምግብ አቅርቦት ችግር ለማቃለል ያግዛል ብለዋል።

በቀጣይም ሌሎች የልማት ድርጅቶችና በጎ ፈቃደኞች ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከ88 ሺህ በላይ ወገኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በሰቆጣ፣ ወለህና ፅፅቃ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!