Fana: At a Speed of Life!

የ2015 ረቂቅ በጀት ለእዳ ክፍያ፣ በጦርነት ለወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ፣ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ እና የሀገር ደህንነት ማስጠበቅ ላይ ያተኩራል -አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) የ2015 የፌደራል መንግስት ረቂቅ በጀት ለእዳ ክፍያ፣ በጦርነት ለወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ፣ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ እንዲሁም የሀገር ደህንነት ለማስጠበቅ ትኩረት በመስጠት የተዘጋጀ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለፁ።

ሚኒስትሩ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው የ2015 የፌደራል መንግስት ረቂቅ በጀት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የ2015 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት ረቂቅ በጀት በፊስካል ፖሊሲ ላይ አሁን የተፈጠረውን ጫና ማቃለል ላይ አተኩሮ መዘጋጀቱን ነው ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ለምክር ቤቱ ያብራሩት።

786 ነጥብ 61 ቢሊየን ብር ሆኖ የቀረበው የ2015 ረቂቅ በጀት ዝግጅት የሀገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ትንበያን መሰረት ያደረገ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

በዚህም በሀገሪቱ ጦርነቱ ቆሞ ምቹ የማክሮ ኦኮኖሚ እንደሚፈጠር ታሳቢ ተደርጓልም ነው ያሉት።
ለጦርነቱ ከፍተኛ የመንግስት ሀብት በመዋሉና በደረቃማ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ተደማምሮ ቀደም ብሎ የነበረው የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ ዝቅ ብሎ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ 6 ነጥብ 6 በመቶ እንደሚመዘገብም ተገምቷል ብለዋል።

በ2015 በጀት ዓመትም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከጉዳት በማገገም 9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት እንደሚመዘገብ እንደተተነበየም ነው ያመላከቱት።

የዋጋ ንረትን በተመለከተም በሚያዚያ ወር ላይ 36 ነጥብ 6 በመቶ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አህመድ፥ ግሽበቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ነጠላ አሃዝ ማውረድ እንደሚከብድ ጠቁመዋል።

በ2015 በጀት ዓመት ላይ አስፈላጊ የፖሊሲና መዋቅራዊ እርምጃዎችን ተግባራዊ በማድረግ የዋጋ ግሽበቱን ወደ 11 ነጥብ 9 በመቶ ለማውረድ መታቀዱን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

በአጠቃላይ ረቂቅ በጀቱ በፊስካል ፖሊሲው ላይ አሁን የተፈጠረውን ጫና የማቃለል መንገድን እንደሚከተል አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የተከሰተውን የተዛባ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን ለማስተካከል ይረዳል ተብሎ የታመነበትን የሀገር- በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መንግስት በተጠናከረ መንገድ ተግባራዊ በማድረጉ ተስፋ ሰጭ የኢኮኖሚ ለውጦች መታየት ጀምረው እንደነበርም አውስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ የተደረጉ መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የተከሰቱትን ተጽዕኖች እና ተግዳሮቶች ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ፈጥረዋልም ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በርካታ ፈተናዎች ሲያጋጥሙት እንደነበር ጠቅሰው÷ ባለፉት 2 ዓመታት የበርካታ የዓለም አገራት የኢኮኖሚ እድገት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱንም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት እና በያዝነው በጀት ዓመት የዋጋ ንረት ባለሁለት አሃዝ እድገት በማሳየቱ የኢኮኖሚው ከፍተኛ ፈታኝ ሆኖ መቀጠሉን አመልክተው÷ በኢኮኖሚው ማሻሻያ ትግበራ አመርቂ ውጤት ያልታየበት የዋጋ ንረት ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር አስፈላጊ የፊሲካል እና የገንዘብ ፖሊሲዎችን እንዲሁም የአቅርቦት የንግድ ስርዓት እና ተያያዥ ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ የተቀናጁ እርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው ያለላከቱት ፡፡

በመንግስት በኩል የዘይት፣ የስኳር፣ የስንዴና የመሳሰሉት የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችን አቅርቦት ችገር ለመፍታት ለድጎማ የሚውል ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ እቃዎቹ ከውጪ በወቅቱ እና ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ በማድረግ የወጋ ንረቱ በህብረትሰቡ ኑሮ ላይ የሚያደርሰውን ጫና በተወሰነ ደረጃ ለማርገብ ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም አብራርተዋል።

በመሆኑም የ2015 ረቂቅ የፌደራል መንግስት በጀት ለእዳ ክፍያ፣ በጦርነት ለወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ፣ በጦርነት እና በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ እንዲሁም የሀገር ደህንነት ለማስጠበቅ ትኩረት እንደሰጠ ነው ያስረዱት።

የበጀት ጉድለት በዚህ ረቂቅ በጀት ላይ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጊዜ ሲነፃፀር ከፍ ያለ መሆኑን ያነሱት አቶ አህመድ፥ ሆኖም በዋጋ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳያሳድር ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል ብለዋል።

የተዘጋጀው ረቂቅ በጀት ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ጭማሪ ያሳየ ቢሆንም ከሀገሪቱ የልማት ፍላጎት አንፃር ግን በቂ አለመሆኑን ሚኒስትሩ አንስተዋል።

በመሆኑም ፈፃሚ አካላት ቁጠባን መሰረት በማድረግ ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም ይገባቸዋል ነው ያሉት።

እነዚህ ፈፃሚ አካላት የመንግስትን የግዢ ስርዓት አክብረው እንዲሰሩ እና ወጪ ቆጣቢ አሰራሮችን እንዲከተሉም አሳስበዋል።

የበጀት አፈፃጸሙ ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቁጥጥሩን አጥብቆ እንደሚቀጥል በመጠቆም፥ በዚህ ቁጥጥር እና ክትትል ውስጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለሚኒስቴሩ ድጋፍ እንዲያደርግም ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ጠይቀዋል።

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.