Fana: At a Speed of Life!

የሩሲያ እና የዩክሬን ኃይሎች በሴቬሮዶኔስክ ከተማ “የከፋ” የተባለውን የጎዳና ላይ ውጊያ እያካሄዱ መሆኑ ተነገረ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 30፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የሩሲያ ወታደራዊ ኃይሎች ሴቬሮዶኔስክ የተባለችውን ከተማ ለመቆጣጠር ከዩክሬን ወታደሮች ጋር የጎዳና ላይ ውጊያ እያደረጉ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡

ትንሿን የኢንዱስትሪ ከተማ ሴቬሮዶኔስክን ለመያዝ እየተካሄደ ያለው ውጊያ ከዚህ በፊት በምሥራቅ ዩክሬን ከተካሄደው ወሳኝ ጦርነት የከፋ እና የሩሲያ ዋና የወታደራዊ ኢላማ እንደሆነችም ተገልጿል፡፡

ምክንያቱም ሩሲያ በአካባቢው ያለውን የሉሃንስ ግዛት በተገንጣዮች ስም ግዛቲቱን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ስለምትሻ ነው ይላል የሬውተርስ ዘገባ።

ሩሲያ ወታደራዊ ትኩረቷን ወደ ዶንባስ ግዛት በማድረግ የኢንዱስትሪ ከተማ በሆነችው ሴቬሮዶኔስክ አካባቢ የሚገኙና ወታደራዊ ፋይዳ ያላቸውን ቦታዎች መቆጣጠሯን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ ተናግረዋል፡፡

የሩሲያ ጦር 97 በመቶ የሚሆነውን የሉሃንስክ ግዛት ነፃ ማውጣቱን ሚኒስትሩ የተናገሩ ሲሆን፥ እስካሁን በነበረው ውጊያ 6 ሺህ 489 የዩክሬን ወታደሮች እጅ መስጠታቸውን አመላክተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሉሃንስክ ግዛትን ሙሉ በሙሉ ለመቀቆጣጠር በሚደረገው ውጊያ የዩክሬን ወታደሮች በሴቬሮዶኔስክ ከተማ በሚገኙ ጎዳናዎች ጠንካራ የመከላከል ውጊያ እያደረጉ እንደሆነ ነው የተገለጸው።

ደም አፋሳሽ በተባለው በዚሁ የሴቬሮዶኔስክ የጎዳና ላይ ውጊያ የዩክሬን ወታደሮች በመልሶ ማጥቃት የሩሲያን ወታደሮች ግስጋሴ ለመግታት እየሞከሩ ነው ተብሏል፡፡

የዩክሬኑ ፕሬዚዳነት ቭሎዶሚር ዘለንስኪ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ጀግኖቻችን በሴቬሮዶኔስክ ያሉ ይዞታቸውን አይለቁም ብቻ ሳይሆን የተያዙባቸውን ሌሎች ግዛቶቻቸውንም ተጋድለው ያስለቅቃሉ” ሲሉ ሰራዊታቸውን አወድሰዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ዛሬ ከእንግሊዙ የፋይናንሺያል ታይምስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥“እየተዋጋን ያለነውና ያን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈልነው ግዛታችንን ለማስገንጠልና አገራችንን ለጠላት አሳልፈን ለመስጠት አይደለም” ብለዋል።

ዘለንስኪ ይህን የተናገሩት አራተኛ ወሩን ያስቆጠረው የሩስያ – ዩክሬን ጦርነት መቋጫ ያገኝ ዘንድ ‘ዩክሬን ለሩስያ የተወሰነ ግዛት መስጠት አለባት ‘ የሚሉ አስተያየቶች በሰፋት እየተነገሩ በመሆኑ ለዚያ ምላሽ ለመስጠት ጭምር እንደሆነ ጋዜጣው ዘግቧል።

በሴቨርዶኔስክ የዩክሬን ወታደሮች በቁጥር እንደሚበልጡ እና የሩሲያ ወታደሮችን መዋጋት የሚያስችል ቁመና እንዳላቸውም ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት፡፡

ሩሲያ በበኩሏ ዛሬም በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ‘ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን’ እንጂ ‘ጦርነት’ አይደለም እያለች ነው።

የሩሲያ ባለሥልጣናት ከዩክሬን ጋር እያካሄዱ ያሉትን ውጊያም የዩክሬንን ‘ወታደራዊ አቅምን ለማዳከም’ እና ‘የናዚ ስሜትን ለማጥፋት’ የሚካሄድ ‘ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን’ እንደሆነ ነው ዛሬም እየገለጹ ያሉት።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.