የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚ ያደርጋል ብላ እንደምታስብ ታንዛኒያ ገለፀች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣2014 (ኤፍ ቢሲ) ታንዛኒያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚ ያደርጋል ብላ እንደምታስብ የታንዛኒያዋ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ተናገሩ፡፡
በታንዛኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደርና ባለ ሙሉስልጣን ሽብሩ ማሞ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለታንዛኒያ ፕሬዚዳንት አቅርበዋል፡፡
አምባሳደሩ የሹመት ደብዳቤያቸውን ባቀረቡበት ወቅት የሁለቱን ሀገራት የረጅም ዘመናት ግንኙነትና ቀጣይ የትብብር መስኮችን በሚመለከት ከፕሬዚዳንቷ ጋር ሀሳብ ተለዋውጠዋል ።
አምባሳደር ሽብሩ በዚህ ወቅትም በሀገሪቱ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እና መንግስት እየወሰዳቸው ስላሉ እርምጃዎች እንዲሁም ስለ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለፕሬዚዳንቷ ገለፃ አድርገውላቸዋል።
በታንዛኒያ እስር ቤት በአስከፊ ችግር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተለቀው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱም አምባሳደሩ ጠይቀዋል።
ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በአምባሳደሩ ስለቀረበላቸው ገላፃ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር ለመፍታት መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚያደንቁም ተናግረዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በሚመለከትም ግድቡ ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ነው ሲሉ ገልፀዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኘውን የታንዛኒያ ኤምባሲ መሬት ጉዳይ በቅርብ መፍትሄ እንዲያገኝ የኢትዮጵያ መንግስት ያሳለፈው ውሳኔ እንዳስደሰታቸው የተናጉሩት ፕሬዚዳንቷ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዘመን በማይሸር ወዳጅነት የተሳሰረ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በታንዛኒያ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ዜጎች እንዲለቀቁና ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ መንግስታቸው ቀና ውሳኔ እንደሚሰጥበትም አረጋግጠዋል።
የታንዛኒያ ዜጎች በኢትዮጵያ አቪየሽን ዘርፍ ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቷ፥ ለዚህም ኢትዮጵያ በዘርፉ የአፍሪካ ተምሳሌት መሆኗን በመጥቀስ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ያላቸውን አድናቆት መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡