Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ እና ቱርክ ከዩክሬን የእህል ንግድን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መከሩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ እና የቱርክ መከላከያ ሚኒስትሮች ከዩክሬን የእህል ንግድን ወደ ውጭ መላክ በሚቻልበት እና በሶሪያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በስልክ መክረዋል፡፡

ከየካቲት ወር ጀምሮ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተፈጠረው ግጭት ከሀገራቱ በጥቁር ባሕር በኩል በመርከብ ተጭኖ ሲወጣ በነበረው የእህል ንግድ ላይ እንቅፋት ፈጥሯል።

በዚህ ምክንያትም በዓለም አቀፉ የምግብ ፍጆታ በተለይም በጥራጥሬ ግብይት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።

ቱርክ ሀገራቱ የእህል ወጪንግድ፣ የምግብ ዘይት እና ሌሎች የግብርና ምርቶቻቸውን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያቀርቡ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ያላትን ተስፋ መግለጿን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡

የቱርክ መከላከያ ሚኒስትር ሁሉሲ አካር፥ በቀጠናው የሰፈነውን መረጋጋት ለማደፍረስ በሰሜናዊ ሶሪያ በሚንቀሳቀሱ የኩርድ አማጽያን እና አሸባሪዎች ላይ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ ለሩሲያው አቻቸው ሰርጌይ ሾይጉ ነግረዋቸዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትሮቹ የሥልክ ውይይት የተካሄደው የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶኻን ከሁለት ሣምንታት በፊት በቀጠናው በሚንቀሳቀሱ የኩርድ አማጽያን ላይ ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ቱርክ ጥቁር ባሕርን ከሩሲያ እና ከዩክሬን ጋር እንደምትዋሰን ይታወቃል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ጥረት የሩሲያ እና የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአንካራ ተገናኝተው የእህል ወጪ ንግድ ከዩክሬን በመርከብ ተጭኖ መውጣት በሚችልበት እና በሶሪያ ጉዳይ ላይ መምከራቸው ይታወሳል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.