ቻይና አዲስ የጨረቃን ካርታ አስተዋወቀች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣2014 (ኤፍ ቢሲ) ቻይና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጥራት አለው የተባለውን አዲስ የጨረቃን ካርታ አስተዋውቃለች፡፡
ቻይና ያስተዋወቀችው አጠቃላይ የጂኦሎጂካል የጨረቃ ካርታ 1 ለ 2 ሚሊየን 500 ሺህ የካርታ ስኬል መጠን ያለው ሲሆን እስካሁን ከነበሩት የጨረቃ ካርታዎች የበለጠ ጥራት አለው ተብሏል፡፡
የቻይና ተመራማሪዎች ከቻይና የጨረቃ ፍለጋ ፕሮጄክት እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተገኙ መረጃዎች እና የምርምር ግኝቶች ላይ በመመርኮዝ አዲሱን ከፍተኛ ጥራት ያለው የጨረቃ ካርታ ይፋ ማድረጋቸው ተመላክቷል፡፡
ካርታው ስለ ጨረቃ መልክዓ ምድራዊ አቀማምጥ እና ስለ ጨረቃ ዝግመተ ለውጥ መረጃ የሚሰጡ አወቃቀሮች የተገጠመለት ሲሆን ለጨረቃ ሳይንሳዊ ምርምር፣ ለስነ ፈለክ እንዲሁም በጨረቃ ላይ የማረፊያ ቦታ ለመምረጥ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ነው የተባለው፡፡
በቻይና የሳይንስ አካዳሚ የጂኦ ኬሚስትሪ ኢንስቲቲዩት ከቻይና ጂኦ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ እና ሻንዶንግ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የጨረቃ ፕሮጀክቱን በመምራት ሲያስፈፅም እንደነበር ተገልጿል፡፡
ካርታው ግንቦት 30 ሳይንስ ቡሌቲን በተባለው እና በቻይና የሳይንስ አካዳሚ እና ከቻይና ብሄራዊ የተፈጥሮ ሳይንስ ፋውንዴሽን በጋራ በሚደገፈው ሳይንሳዊ መፅሔት ላይ መታተሙ ተመላክቷል፡፡
ቀደም ሲል ዩ ኤስ ጅ ኤስ የተባለው የስነ ከዋከበት ማዕከል በፈረንጆቹ 2020 1 ለ 5 ሚለየን በሆነ የካርታ ስኬል መጠን የጨረቃ ካርታ አጠናቆ ይፋ ማድረጉን ሲ ጅ ቲ ኤን በዘገባው አስታውሷል፡፡