በአማራ እና በአፋር ክልሎች መካከል ያለው የቆየ ግንኙነት እንዲጠናከር የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ እና በአፋር ክልሎች መካከል ያለውን የቆየ እና የዳበረ ግንኙነት እንዲጠናከር እና ሁለቱ ሕዝቦች በጋራ በልማት በሚያድጉበት ጉዳይ ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡
በውይይቱ ኢኮኖሚ፣ ጸጥታ እና የእርስ በርስ ግንኙነት ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች ሲሆኑ÷ የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አጎራባች ዞን መሪዎችም በውይይቱ ተሳትፈዋል፡፡
በውይይቱ ለጋራ ሰላም እና ለልማት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን÷ በተለይም በተደጋጋሚ ብልጭ ድርግም የሚሉ የድንበር ግጭቶችን እንዳይፈጠሩ መስራት፥ ከተፈጠሩም በቶሎ እንዲፈቱ ማድረግ ላይ ከተሰራ ለውጥ እንደሚመጣ ተጠቁሟል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ በተሰጠው መግለጫ÷ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ፥ ሁለቱን ሕዝቦች በማጋጨት ኢትዮጵያን ማተራመስ ለሚፈልጉ እድል ላለመስጠት እና የሁለቱን ህዝቦች ስር የሰደደ እና የዳበረ ሁለንተናዊ ግንኙነት እንዲጠናከር ለማድረግ በወንድማማቾች መካከል በግልጽነት የተደረገ ውጤታማ ውይይት ነበር ብለዋል፡፡
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተሰዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው÷ ትህነግን አሳፍሮ ከመመለስ ጀምሮ አንድ የሚያደርገን የበዛ ሕዝቦች ነን፤ ያሉንን የኢኮኖሚ አማራጮች በጋራ በመሥራት በጋራ ማደግ አለብን ብለዋል፡፡
“ሁለታችንም የሚፈጠሩ ትንንሽ የድንበር ግጭቶችን በፍጥነት በመፍታት በትህነግ ያፈረሰብንን መገንባት እና በጋራ በማደግ እኛን በማጋጨት ኢትዮጵያን መበጥበጥ የሚፈልግጉትን ሁሉ ማሳፈር አለብን” ሲሉ አቶ አወል አርባ ተናግረዋል፡፡
ውይይቱ ውጤታማ እንዲሆን እስከ ቀበሌ ወርዶ ሁሉም ድርሻውን አውቆ እንዲሰራ ይደረጋል መባሉንም አሚኮ ዘግቧል፡፡