Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ከ516 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የግብርና ማሽነሪዎችን በመገጣጠም ወደ ኢኮኖሚው አስገብቷል

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ የአዳማ የግብርና ማምረቻ ኢንዱስትሪ ባለፉት 6 ወራት ከ516 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የግብርና ማሽነሪዎችን በመገጣጠም ወደ ኢኮኖሚው እያስገባ መሆኑ ተገለፀ።

ከእነዚህ ውስጥ በ2014 ዓ.ም ከ277 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ ለበልግና ለመኸር እርሻ አገልግሎት የሚሆኑ የተለያዩ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ትራክተሮች ፣ የትራክተር ተቀፅላ መሳሪያዎች እንዲሁም የተለያዩ የውሃ ፓምፖችን በመገጣጠም በመላ ሀገሪቱ ግዥለመፈፀም ጥያቄ ላቀረቡ አካላት ማስረከብ መቻሉን የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አምባሳደር ምስጋናው አረጋ ተናግረዋል ።

በዚህም የሶማሌ ክልልን ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የከፋ ዞን አስተዳደርና ለሌሎችም ተቋማትና ባለሀብቶች ማሽነሪዎች ማቅረብ ተችሏል ነው የተባለው።

የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ አዳማ አዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ወደሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲገቡ ካደረጋቸው ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች ባለፈ 239 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የተለያዩ ትራክተሮች ጥያቄ ቀርቦ ስራዎች እየተሰሩ ነው ተብሏል ።

ከዚህ ባለፈም ኢንዱስትሪው 3 ሺህ 400 በላይ ትራክተሮችን እና 318 የተለያዩ አቅም ያላቸው የውሀ ፓምፖችን ማምረት የሚያስችል ጥሬ እቃዎች ያሉትና እነዚህንም ወደ ኢኮኖሚው ለማስገባት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ወደ ሪፎርም ስራ እንዲገባ አቅጣጫ የተቀመጠለት ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ የመንግስት የልማት ድርጅት በስሩ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎች ያሉት ሲሆን ÷ በግብርና ማሽነሪ ዘርፍ ስር ያለው የአዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንድስትሪም አንዱ ነው።

በኢንዱስትሪው ለረጅም አመታት በአሰራር ችግር ምክንያት ኢኮኖሚው ውስጥ ሳይንቀሳቀሱ የቆዩ የተለያዩ ማሽነሪዎችን አሁን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ላይ አወንታዊ ሚና እንዲጫወቱ እየተሰራ መሆኑን አምባሳደር ምስጋናው ገልጸዋል።

በግብርና ሴክተሩ ላይ በተለይ የበጋ ስንዴን ማምረት ላይ የተሻለ ውጤት መገኘቱን ያነሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው ይህን እንቅስቃሴ በሰፊው በማሽነሪዎች ቢደገፍ ደግሞ ከአሁኑ የተሻለ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል።

በፀጋዬ ወንድወሰን

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.