ለመሰረተ ልማት ስራዎች ውጤታማነት የተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከርና ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለፀ።
ሚኒስቴሩ ከክልልና ከከተማ መስተዳድሮች ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት በመሰረተ ልማት ቅንጅታዊ አሰራር ዙሪያ በሐረሪ ክልል የግንዛቤ መስጫ መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የከተማና መሠረት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ አንደገለጹት÷ በሀገሪቱ ከመሰረተ ልማት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በአግባቡ መፍታት እንዲቻል መድረኩ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።
በሀገሪቱ ባለፉት አስርት ዓመታት በመንገድ፣ በቴሌኮም፣ በባቡርና በመብራት ዘርፍ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አንስተው፥ በዘርፉ የቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር በሀገሪቱ ሀብት ላይ ብክነት መፍጠሩን ተናግረዋል ።
መሠረት ልማቶችን መገንባትና ማደስ ብቻ ሳይሆን ቅንጅታዊ አሰራር ላይ ማተኮር እንደሚገባ የተናገሩ ሲሆን÷ ለማህበረሰቡ ኑሮ መሻሻልና ለሀገሪቱ ልማት መፋጠን የመንገድ፣ ውሃና ኤሌክትሪክ የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል ።
የሀረሪ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪም በበኩላቸው÷ በተለይ ከመንገድ ስራ፣ ከኤሌክትሪክ ዝርጋታና ከቴሌኮሙኒኬሽን ጋር ተያይዞ ስራዎችን አቀናጅቶ መምራት በዘርፉ ከዋጋ፣ከጥራትና ከጊዜ አኳያ የተሻለ ጥቅም እንደሚያስገኝም ገልጸዋል ።
በመድረኩ ላይ የሀረሪ፣ የሶማሌ፣ የአፋርና የድሬዳዋ ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የተገኙ ሲሆን÷ በቀጣይ በመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ዙሪያ የጋራ እቅዶች ቀርበው ውይይቶች ይደረግባቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከሐረሪ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!