የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች የጋራ መድረክ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት እና የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች የጋራ መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
የጋራ መድረኩ በዛሬው ውሎው የፓርቲውን የ10 ወራት የስራ አፈፃፀም መገምገሙን ከፓርቲው ዋና ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በመድረኩ የብልጽግና ፓርቲ ባለፉት 10 ወራት ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ በጥልቀት መገምገሙ ተመላክቷል፡፡
በሂደቱ የተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች የተለዩ ሲሆን ÷ በቀጣይ በልዩ ትኩረት መከናወን የሚገባቸው የፓርቲና አገራዊ ቁልፍ ስራዎች መለየታቸውም ተጠቁሟል፡፡
የውይይት መድረኩን የመሩት የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ባደረጉት ንግግር ÷ የተገኙ ድሎችን አጠናክሮ ማስቀጠልና ጉድለቶችን ማረም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡