ሩሲያ ለዓለም ሁለንተናዊ ደኅንነት ስትል ጦርነቷን ታቁም ስትል ዩክሬን ጠየቀች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለዓለም ሁለንተናዊ ደኅንነት ሲባል ሩሲያ የምታካሂደውን ጦርነት ታቁም ስትል በእስያን ሀገራት የመከላከያ ጉባዔ ላይ ዩክሬን ጠየቀች።
በሲንጋፖር በተካሄደው የእስያ ሀገራት ቀጣናዊ የደኅንነት እና የመከላከያ ጉባዔ ÷ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከምስጢራዊ ቦታ ሆነው በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የጦርነቱ ጦስ ሀገራቸውን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ሥርዓት እንደሚያናጋው ማስጠንቀቃቸውን ዘ ስትሬይትስ ታይምስ ዘግቧል፡፡
ዘለንስኪ ኃያላን ሀገራት ታዳጊዎቹን እንደፈለጉ ቢያጠቁ እና ዓለም አቀፍ ሕግ ባይኖር ዓለም እትጠፋለች” በማለት በበይነ መረብ ባደረጉት የ10 ደቂቃ ንግግራቸው ÷ “ዓለምአቀፍ ሕግ ባይኖር ኖሮ እና ትልቁ ዓሳ ትንሹን ቢበላ ፣ ትንሹም ዓሳ ከእሱ ያነሱ ትንንሾቹን ቢበላ ማናችንም አንተርፍም ነበር” ብለዋል፡፡
ዘለንስኪ አክለውም ÷ የእስያ ሀገራት ድጋፋቸውን ለዩክሬን መስጠት እንዲቀጥሉና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከምግብ አቅርቦት ወጭ ንግድ ለማሳለጥ ሩሲያ የዘጋችውን የባህር ወደብ እንድትከፍት ግፊት አንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ይህ ካልሆነ ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም እስያ እና አፍሪካ ለከፋ የምግብ ዕጥረት እና ለረሃብ እንደሚጋለጡ አስጠንቅቀዋል ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ፡፡
በዚህ ዓመት የእስያ ሀገራት ቀጣናዊ የደኅንነት እና የመከላከያ ጉባዔ ላይ ከ 40 እስያ ሀገራት የተውጣጡ 575 ተወካዮች ተካፍለዋል፡፡