Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 9 ወራት 10 ሚሊየን ሴቶች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል – ዶክተር ደረጀ ዱጉማ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 9 ወራት ከ10 ሚሊየን የሚበልጡ እናቶችን የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ÷ የተመጣጠነና ደስተኛ ቤተሰብ ለመመስረትና የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ወሳኝ በመሆኑ መንግስት ለፕሮግራሙ ልዩ ትኩረት መስጠቱን በድሬዳዋ አስተዳደር በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮዽያ 50 በመቶ የሚሆኑ ልጃገረዶች 18 ዓመት ሳይሞላቸው እንደሚዳሩና ከእነዚህ ውስጥ 80 በመቶ ያህሉ 20 ዓመት ሳይሞላቸው አርግዘው እንደሚወልዱ ዶክተር ደረጄ ገልፀዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር ለቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት በተሰጠው ልዩ ትኩረት በከተማና በገጠር የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች 44 በመቶ ማድረስ እንደተቻለና 80 በመቶ የሚሆኑ ነብሰ ጡር እናቶች በጤና ተቋማት እየወለዱ መሆኑ በምክክር መድረኩ ላይ ተገልጿል።

የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር÷ የእናቶችና የሕጻናትን ጤና ለማሻሻል የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፥ አስተዳደሩ አገልግሎቱን ለማሻሻልና ተደራሽ ለማድረግ አስፈላጊውን በጀት መመደቡን ተናግረዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ በበኩላቸው ÷ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ለማሻሻልና ተደራሽ ለማድረግ በተሠራው ሥራ ለተገኘው ውጤት የአስተዳደሩ ካቢኔ ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች እገዛ ከፍተኛ እንደነበር ጠቁመዋል።

በኢትዮዽያ በየዓመቱ እስከ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሕጻናት እንደሚወለዱ በምክክር መድረኩ የተጠቆመ ሲሆን፥ ይህን የህዝብ ዕድገት የተመጣጠነ ለማድረግ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ወሳኝ እንደሆነ ነው የተገለጸው።

በድሬዳዋ አስተዳደር የቤተሰብ ዕቅድ አተገባበር ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማትና ባለድርሻ አባላት እውቅና ተሰጥቷል።

በተሾመ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.