የዓለም ባንክ ለአዲስ አበባ ተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር 25 ሚሊየን ዶላር ለመስጠት ወሰነ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም ባንክ ለአዲስ አበባ ከተማ ተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር 25 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለመስጠት ወሰነ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ዳይሬክተር ካሮላይን ተርክ ጋር ተወያይተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በፌስቡክ ገፃቸው እንዳስታወቁት፥ የገንዘብ ድጋፉ ለትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ማህበራዊ መሰረተ ልማት ለማቅረብ የሚውል ነው።
ዓለም ባንክ ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ የከተማ ልማት ሴፍቲኔት መርሃ ግብር አካል መሆኑንም አስታውቀዋል።
የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ካሮላይን ተርክ በበኩላቸው፥ ባንኩ የከተማ አስተዳደሩ እያከናወናቸው ያሉ የልማት ስራዎችን በቀጣይነት እንደሚደግፍ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮው በጀት ዓመት 300 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎችን የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ማድረጉ ይታወቃል።
ይህ የምገባ መርሃ ግብር ዘላቂነት እንዲኖረው ለማስቻልም የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ እንዲቋቋም ማድረጉም ይታወሳል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision